ሶስት ድልድዮችና 176 ኪሎ ሜትር መንገድ ተጠግነው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል

191

ደሴ ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት የተሰበሩ ሶስት ድልድዮችን ጨምሮ 176 ኪሎ ሜትር የተበላሸ መንግድ በመጠገን ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ ዲስትሪክት አስታወቀ፡፡

በዲስትሪክቱ የመንገድ ኔትዎርክና ደህንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጅነር ቃል ኪዳን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት በተለያዩ ችግሮች የሚበላሹ መንገዶችና ድልድዮችን ፈጥኖ በማስተካከል ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

በዚህ ዓመትም በተለያየ ምክንያት የተበላሸ 176 ኪሎ ሜትር መንገድ ተጠግኖ ለትራንስፖርት ምቹ ተደርጓል፡፡

ጥገና ከተደረገለት መንገድ መካከል ኮምቦልቻ- መካነሰላም- ግንደ ወይን፣ ደሴ – ከሚሴ፣ ወልድያ- ፍላቂት፣ ሚሌ – ጋዳፊና ሌሎችም ይገኙበታል ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በአሸባሪው ህወሃት የተሰበሩ ሦስት ድልድዮችም ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካላቸው የጎላ ጠቀሜታ አንጻር መልሰው በፍጥነት ተገንብተውና ተጠግነው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።

ድልድዮቹ ከወልድያ – ቆቦ – መቀሌ በሚወስደው መንገድ “አልውሃ”፣ ከወልዲያ – ድሬ ሩቃ- ጭፍራ በሚወስደው መንገድ “ጨረቲ እንዲሁም ውጫሌ መግቢያ ላይ የነበሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

ለተደረጉት ከባድ፣ ወቅታዊ፣ ድንገተኛና መደበኛ ጥገናዎችም ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ኢንጅነር ቃልኪዳን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሳምሶን ተስፋዬ በበኩላቸው ኮምቦልቻ – መካነሰላም – ግንደ ወይን ያለው መንገድ ጉዳቱ ከፍ ያለ በመሆኑ ከጥገናው ጎን ለጎን በአዲስ መልኩ ደረጃውን አሻሽሎ ለመገንባትም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሚቀጥለው ዓመት ስራቸውን ከሚጀመሩ መንገዶች መካከል አንዱ እንዲሆን ተወስኖ የዲዛይንና የሌሎች ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ህብረተሰቡም ለመንገድ ግንባታው ትብብር በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል ስራ አስኪያጁ፡፡

በ”ጨረቲ” ድልድይ መሰበር ምክንያት ከጅቡቲ-ሚሌ-ጭፍራ-ወልድያ የምናደርገው ጉዞ በመስተጓጎሉ በኮምቦልቻ ደሴ አድርገን የ100 ኪሎ ሜትር መንገድ ጭማሬ ለመጓዝ ተገደን ነበር ያለው ደግሞ አሽከርካሪ ጌታቸው ካሳ ነው፡፡

ድልድዩ በፍጥነት ተሰርቶ ለአገልግሎት ክፍት በመደረጉ “አላስፈላጊ ወጭና እንግልት አስቀርቶልናል” ብሎ፤ በዚህም ደስተኞች መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

ሌላው የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ከድር አሊ በሰጡት አስተያየት ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ መካነ ሰላም ሲጓዙ መንገዱ በመበላሸቱ ከመንገላታታቸው ባለፈ 110 ብር የነበረውን ታሪፍ እስከ 400 ብር ይከፍሉ እንደነበር አውስተዋል።

አሁን ላይ ጥገና እየተደረገለት መሆኑና የተወሰነ መሻሻል ማሳየቱን ጠቁመው፤ የመንገዱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ታይቶ በዘላቂነት ተሻሽሎ በአዲስ ሊገነባ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ ዲስትሪክት በምስራቅ አማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በከፊል ከ2 ሺህ 880 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ እያስተዳደረ እንደሆነም ታውቋል።