የመጪውን ክረምት ወቅት የአየር ጠባይ መረጃን በመገንዘብ የጎርፍ አደጋ ስጋቶችን ለመቋቋም ዝግጅት ያስፈልጋል

149

ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)የመጪው ክረምት ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያ መረጃን በአግባቡ ተገንዝበው ሊኖሩ የሚችሉ የጎርፍ አደጋ ስጋቶችን ለመቋቋም የቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስገነዘበ።

ኢንስቲትዩቱ ከሁሉም ክልሎች ከተወጣጡ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሴክተሮች አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎችና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በአዳማ ከተማ እየመከረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ጠባይ አገልግሎት ተመራማሪ ዶክተር አሳምነው ተሾመ እንደገለፁት የመጪው ክረምት ወቅት የአየር ሁኔታዎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች እንዳይፈትኑ ተገቢውን የቅድመ ጥንቃቄ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የአየር ጠባይ የመረጃ አገልግሎቱን ጥራትን በጠበቀ መልኩ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው ያሉት።

May be an image of 2 people, people sitting, people standing, table and indoor

በተለይም በመጪው ክረምት ሊኖር የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከልና ተፅዕኖውን ለመቋቋም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄና የቅድመ ዝግጅት ስራ ዙሪያ ለመምከር የተዘጋጀ መድረክ መሆኑም ተነግሯል ።

በዚህም በመጪው ክረምት ወቅት የአየር ሁኔታ መረጃን በትክክል እንዲረዱ ከማድረግ ባለፈ ተጋላጭ የሆኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሴክተሮች የጋራ አቅጣጫ በማስቀመጥ ርብርብ ለማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል።

በተለይ ግብርና ፤ጤና፤ውሃ፤አደጋ መከላከል እና ስራ አመራር ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ሴክተሮች በቅንጅትና በትብብር በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት ያስፈልጋል ብለዋል።

የፓስፊክ ውቅያኖስ ከመጠን በላይ እየቀዘቀዘ በመምጣቱ የመጪው ክረምት ዝናብ ሁኔታ ከፍተኛ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ 85 በመቶ የሀገሪቷ አካባቢ የሚሸፍን ስርጭት ይኖራል ነው ያሉት።

የእርሻ ማሳዎች ላይ ደለል እንዳይተኛ፤አፈሩ በጎርፍ እንዳይጠረግ ማድረግ፤የኮትቻ አፈር የእርሻ ማሳዎች ቀድመው በሰብል እንዲሸፈኑ ማስቻል ከግብርና ሴክተሮች ይጠበቃል ብለዋል።

ውሃ ማቆርና መያዝ፤በግድቦች አካባቢ ጉዳት እንዳይኖር የተፋሰሶች ልማትና የውሃ ሴክተሮች የተቀናጀ የዝግጅት ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

የክረምት ወቅትን ተከትሎ ከጤና ስጋት ጋር በተያያዘ ተገቢው ዝግጅትና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በየደረጃው ያሉ ለአየር ንብረት ተጋላጭ የሆኑ ሴክተሮች ከወዲሁ የጋራ አቅጣጫ ይዘው በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም