ፌዴሬሽኑ የወጣቶችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በተቀናጀ አሰራር ለመምራት የሚያስችል ሥምምነት ተፈራራመ

138

ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የወጣቶችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በተቀናጀ አሰራር ለመምራት የሚያስችል ሥምምነት በወጣቶች ላይ ከሚሰራ አንድ ግብረ ሰናይ ተቋም ጋር ተፈራረመ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጽጌረዳ ዘውዱ ከዩዝ ኔትወርክ ፎር ሰስተነብል ዴቨሎፕመንት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢሳያስ አለማየሁ ጋር ተፈራርመዋል።

የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ጽጌረዳ ዘውዱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሥምምነቱ በተበታተነ መልኩ የሚሰሩ ሥራዎችን በቅንጅት ለመምራት የሚያስችል ነው።

በኢትዮጵያ የወጣቶችን ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑንም ነው የገለጹት።

ሥምምነቱም በወጣቶች ዙሪያ በተያዘው አገር አቀፍ የ10 ዓመት የልማት እቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ያስችላልም ነው ያሉት።

ሥምምነቱ በጋራ መርሃ ግብሮችን መንደፍ፣ መተግበር፣ መከታተልና መገምገም እንዲሁም የፋይናንስ መዋቅራዊና ሌሎች ተግባራትን የያዘ መሆኑን አመላክተዋል።

ሥምምነቱ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን በመግለጽ።

የዩዝ ኔትወርክ ፎር ሰስተነብል ዴቨሎፕመንት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ አለማየሁ በበኩላቸው ድርጅቱ በመላው ኢትዮጵያ ባሉት ቅርጫፎች ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየሰራ ነው።

ወጣቶች በሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም አቅማቸውን በሚያሳድጉ የሥልጠና ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

ወጣቶችን ማብቃት፣ የማኅበረሰብ ንቅናቄ፣ የፖሊሲ ቅስቀሳና የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞችን በተለያዩ ደረጃዎች ሰፋ ያሉ ፕሮግራሞችን በጋራ እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

ሥምምነቱ ድርጅቱ እየሰራቸው ያሉ ሥራዎችን ለማጠናከር እንደሚያገዝ ገልጸው ለተፈጻሚነቱም በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።