በዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ የሚፈተነውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም በምርትና ተወዳዳሪነት ላይ ያተኮረ የሥራ ባህል ማዳበር ይገባል

89

ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ) በዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ የሚፈተነውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም ተቋማት በምርትና ተወዳዳሪነት ላይ ያተኮረ የሥራ ባህል ማዳበር እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ "አገራዊ አምራችነት" በሚል ርዕስ ተካሂዷል።

በመድረኩም የኢንዱስትሪ ኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ ምሁሩ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተመራማሪው ዶክተር ታምራት ኃይሌ የመወያያ መነሻ ኃሳብ አቅርበዋል።

የዓለምን ተለዋዋጭ ሁኔታ ተከትሎ የአገራት ኢኮኖሚ በእጅጉ እየፈተነ መሆኑን ፕሮፌሰር ዳንኤል በጽሑፋቸው አብራርተዋል።

በቅርቡ የተፈጠረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በዚህ ረገድ የሚጠቀስ አብነት መሆኑንም ተናግረዋል።

የሁለቱ አገሮች ጦርነት ደግሞ የዓለምን የገበያና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አለመረጋጋት አስከትሏል።

በዚህም ብዙ አገሮች እየተፈተኑ በመሆኑ ችግሩን ለማለፍ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም የዚሁ ዓለም አቀፍ ቀውስ ገፈት ቀማሽ በመሆኗ የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን በመከተል ከተጽዕኖው ለመሻገር ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በዘላቂነት ለመቋቋም አገራዊ አምራችነትን ማሻሻል ልዩ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በሥራ ባህል ላይ ያለው የልቦና ውቅርም ሊሻሻል ይገባል ያሉት ፕሮፌሰር ዳንኤል በተለይ ተቋማት አምራችነትና ተወዳዳሪነት ላይ ትኩረት ያደረገ የሥራ ባህል መገንባት አለባቸው ብለዋል።

በዚህም የዓለምን ተለዋዋጭ ተጽዕኖ መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተመራማሪው ዶክተር ታምራት ኃይሌ በበኩላቸው፤ ባለፉት 100 ዓመታት በዓለም የተከሰተው ተለዋዋጭ ሁኔታ አገራት ለአምራችነት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረጉን አስረድተዋል።

በዓለም ላይ ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነቡ አገራት ተሞክሮ የሚያሳየው አምራችነትን ማሻሻል ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ዜጎች ጉዳይ ሆኖ መስራቱን ነው።

ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ኢትዮጵያዊያን በትብብር አምራች የሆነ የሥራ ባህል መገንባት አለባቸው ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከመንግሥት ጎን ለጎን የግል ባለሃብቱም ምርትን በጥራትና በብዛት ማምረት እንደሚገባ ጠቁመው  በዚህም የምርትን ተወዳደሪነት ማረጋገጥ ሊተኮርበት ይገባል ብለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም