በክልሉ ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶች ሚና የጎላ ነው – ቢሮው

96

ሚዛን አማን፤ ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ)፡ በክልሉ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶች ሚና የጎላ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮው አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ  በክልሉ በሚገኙ የሸካ፣ ምዕራብ ኦሞና ቤንች ሸኮ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ላለፉት ሦስት ዓመታት የጸጥታ ችግር መከሰቱን አስታውሰዋል።

ክልሉ ከተዋቀረ በኋላ አመራሩ ህዝቡን በማሳተፍ የተሰራው ሥራ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ ማስቻሉን አመልክተዋል።

በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የህዝብ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ሃላፊው፤ ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶችን በመጠቀም ግጭቶችን መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች ሸፍተው ግጭት የመፍጠር ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትን በሽምግልና ሥርዓት እንዲያግባቡ በማድረግ የተሰራው ሥራ  ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡን በማወያየት በተሰራው ሥራ በምዕራብ ኦሞ ዞን ለሦስታት ዓመት መንገድ ዘግተው ተለያይተው የነበሩ የሱሪና ዲዙ ወረዳ ነዋሪዎችን ወደ ቀድሞ አንድነታቸው መመለስ መቻሉን  ጠቅሰዋል።

ቴፒ  ከተማ እና ጉራፈርዳ ወረዳ ላይ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በሰራው ሥራ አንጻራዊ ሰላም መታየቱን አመልክተዋል።

 የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል በጫካ የሚገኙ ሽፍቶችን በሽምግልና አልያም በጸጥታ ኃይል የማስወጣት ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው ክልሉ ከመዋቅሩ በፊት የግጭት ቀጠና እንደነበር አስታውሰው ሕዝባዊ ውይይቶችና ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ክልሉ የነበረበትን የግጭት ጫና መቀነስ ማስቻላቸውን ተናግረዋል።

ታጥቀው ጫካ የገቡ ሽፍቶች የአካባቢው ነዋሪዎችን እርስ በእርስ  እንዲጋጩ በማድረግ በንጹሐን ወገኖች ላይ ዘረፋ፣ ግድያና መፈናቀልን ያደርሱ እንደነበር ጠቁመዋል።

ክልሉ ባለፉት አራት ወራት የግጭት ሪፖርት ያልቀረበበት መሆኑን አመልክተው፤ አመራሩ የግጭት ማስወገጃና ሰላም ግንባታን  ከባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶች ጋር በማስተሳሰር መፈጸሙ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

በክልሉ  የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጠል ክልሉ የጀመረው የባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል ።

ሌሎች ክልሎች ይህን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ በአካባቢያቸው የሚገኙ ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶችን  ጥቅም ላይ በማዋል ሰላማቸውን እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።

በየማህበረሰቡ ያሉ ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶችን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህገ ወጥ ተግባራትን የሚፈጸሙ አካላትን ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ተመክረው በማይመለሱ አካላት ላይ  እርምጃ በመውሰድ “የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ  ይሰራል” ብለዋል ።

በሚዛን አማን ከተማ በተለያዩ የጸጥታና ሰላም ጉዳዮች የመከረው የሰላም ሚኒስቴር መድረክ የቀጣይ ትኩረት ያላቸውን አቅጣጫዎች በማስቀመጥ መጠናቀቁ ይታወሳል።