ቻይና የብሪክስ አባል ሀገራት ግጭት ቀስቃሽ ሁኔታዎችን በመከላከል ለአለም ደህንነትና ሰላም እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበች

143

ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ የብሪክስ አባል ሀገራት ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ሁኔታዎች ከቀዝቃዛ ጦርነት እሳቤ በመውጣት ለአለም ደህንነትና ሰላም እንዲሰሩ ጥሪ አቀረቡ።

ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ቻይና አባል በሆነችበት የብራዚል፣ ሩስያ፣ህንድና ደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ጥምረት (ብሪክስ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ እና በተለያዩ የአለም ክፍሎች የታዩ ግጭቶች ከዚህ በፊት ከነበሩት ሁኔታዎች በባሰ አስከፊ ችግሮችን አስከትለዋል ብለዋል።

ይህንን ችግር ለመቋቋም የብሪክስ አባል ሀገራት ትልቅ አቅም መሆናቸውን ገልጸው ልማትን፣ ሰላምን፣ እኩል ተጠቃሚነትንና ዴሞክራሲን ለማስፈን ተጨባጭ ስራዎችን መስራት ይገባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

አባል ሀገራቱ የሚተገብሩት አወንታዊ እርምጃ በአለም ላይ የሚታየውን አስከፊ ሁኔታ የመቀየር አቅምም አለው ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ዢ ጂንፒንግ በሌሎች ሀገራት ሉአላዊነት ላይ የሚቃጡ እንቅስቃሴዎች በታሪክ አስከፊ ሁኔታዎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ ሲሉ አሳስበው የብሪክስ አባል ሀገራት በደህንነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ጠንክረው መስራት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት የእኔ እበልጥ ፖለቲካዊ አተያይና የቀዝቃ ጦርነት እሳቤንም በመከላከል ለአለም ህዝቦች ደህንነትና ሰላም እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ሲጂቴኤን ዘግቧል።