የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ30 ሺህ በላይ አባላቶቹን ለማሳተፍ መዘጋጀቱን ገለጸ

171

ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ30 ሺህ በላይ አባላቶቹን ለማሳተፍ መዘጋጀቱን ገለጸ።

ለክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ የመለየት፣ ወጣቶችን የመመልመል፣ የመመደብና ከተቋማት ጋር የማስተሳሰር ተግባር በማከናወን ላይ መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ፀሐፊ ይሁነኝ መሃመድ፤ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ ማህበሩ ከረዥም ጊዜ አንስቶ በክረምት እና በበጋ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ይናገራል።

በክረምቱ ደግሞ በርካታ ወጣቶችን የማግኘት እድል ስላለው ከ30 ሺህ በላይ አባላቱን በማሳተፍ የተለያዩ የበጎ ሥራ የስምሪት መስኮችን በማመቻቸት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአካባቢ ጽዳትና ውበት፣ ስፖርት፣ ኪነ-ጥበብ፣ የችግኝ ተከላ፣ የትራፊክ ፍሰት ማስተናበርን ጨምሮ የሰላምና የፀጥታ ሥራዎች በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶቹ ይከወናሉ ብሏል።

በተለይ የአብሮነትና የአንድነት እሴቶችን የሚያጠናክሩ መርሃ-ግብሮችን ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግም ማሕበሩ የሚሳተፍበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሆኑን አብራርቷል።

የበዓላት ወቅት የማዕድ ማጋራትና የቤት እድሳት በዋነኝነት የሚተገበሩ ይሆናሉ ብሏል።

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመደገፍ ሃብት የማሰባሰብ ሥራም በማህበሩ የሚካሄድ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ገልጿል።

የደም ልገሳ፣ የጽዳት፣ የአካባቢ ማስዋብና እድሳት ሥራዎች የሚከናወኑ ይሆናል።

የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ ረገድ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቅሷል።

ከማህበሩ አባላት በተጨማሪ ሌሎች የከተማዋ ወጣቶች ክረምቱን ለበጎ ተግባር በማዋል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

በአዲስ አበባ በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።