የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋለውን የአዋጭነት ጥናትና የዲዛይን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው

126

ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በመስኖ ፕሮክቶች የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ የምክክር አውደ ጥናት በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ነው።

አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ ኢንጂነር ሳሙኤል ሁሴን መንግሥት ለመስኖ ልማት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም 18 ቢሊዮን ብር በመመደብ የትላልቅና የአነስተኛ ግድቦች ግንባታ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ዘርፉ አሁንም ችግሮች እንዳሉበት ያነሱት ኢንጂነር ሳሙኤል: በአነስተኛና ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የአዋጭነት ጥናት፣ የዲዛይንና የግንባታ መጓተት ፈተና መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

በዚህም ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀትና ጥራት ለማጠናቀቅ አለመቻሉን በማንሳት የፕሮጀክቶች አለመጠናቀቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዛሬው የምክክር አውደጥናት ዋና ዓላማም በፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩ የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ነው።  

ፕሮጀክቶቹ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሚገነቡበት አካባቢን የሥነ-ምህዳር፣ የውሃና የአፈር እንዲሁም የአየር ሁኔታን ለማጥናትና የጂኦስፓሻል መረጃዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአውደጥናቱ የስፔስ ሳይንስ፣ የጂኦስፓሻልና የሜትሮሎጂ ቴክኖሎጂዎችና መረጃዎች ለመስኖ ፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ያላቸው ፋይዳ ላይ ያተኮሩ የመወያያ ፅሁፎች ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በመጡ ተመራማሪዎች በመቅረብ ላይ ናቸው።

አውደ ጥናቱ ለአንድ ቀን የሚቆይ ሲሆን የመስኖ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ተቋራጮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም