የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

213

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ ጋር በፀሐይ ኃይል ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ።

ኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ  የፀሐይ ብርሃን በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ከ100 በላይ ሀገራት በይነ መንግስታት ጋር  በጋራ የሚሰራ ተቋም ነው።

በዛሬው እለትም በሶላር ኢነርጂ  ልማት ላይ በትብብር መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢፌዴሪ የውሃና ኢነርጂ  ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል።

በሶላር ኢነርጂ የሚሰሩ ለመስኖ ልማትና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውሉ ፓምፖችን ለማቅረብና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ በስምምነቱ መካተቱ ተገልጿል።

የፕሮጀክቱ ትግበራ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማሳለጥ  የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ፤ የጋራ ስምምነቱ በተለይ የገጠሩ ኅብረተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የዛሬው ስምምነትም የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል።

የጋራ ስምምነቱ የኢኮኖሚ ልማትን ለማፋጠንና የመስኖ ልማት ሥራን ውጤታማ ለማድረግ አጋዥ መሆኑ ተገልጿል።

በተለይም በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች የፀሐይ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ሲሆን  ለአቅም ግንባታ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ጠቃሚ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ  (አይ.ኤስ .ኤ) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አጄይ ማቱር፤  በሶላር ኢነርጂ ዘርፍ በኢትዮጵያ ሰፊ ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመስራት ፍላጎት አለን ብለዋል።

ኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ በቀጣይም ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር ስምምነቶችን እንደሚፈራረም ይጠበቃል።                                            

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም