ዩኒቨርሲቲው የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላምና የመከባበር ባህልና እሴት እንዲያጎለብቱ ይሰራል

115

ደሴ ግንቦት 11/2014 /ኢዜአ/  መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የወሎን የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላምና የመከባበር ባህልና እሴት እንዲያጎለብቱ እንድሚሰራ አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ካሳ ሻውል ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው አዲስ የተመደቡ 4ሺህ 500  ተማሪዎችን ከትናንት ጀምሮ እየተቀበለ ነው።

አዲስ ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆን ከማገዝ ጎን ለጎን የወሎን የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላምና የመከባበር ባህልና እሴት ተምረው ለሌሎችም እንዲያስተምሩ ይሰራል ብለዋል፡፡

ተማሪዎች አንድነታቸውንና ሰላማቸውን ጠብቀው ለሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአሸባሪው ህወሓት ውድመት ቢደርስበትም በተቀናጀ አግባብ መልሶ በማቋቋም ተማሪዎችን መቀበል እንደተቻለ ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከተመደቡ ተማሪዎች ውስጥ 55 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው ብለዋል።

ተማሪዎቹ በቱሉ አውሊያና መካነሰላም በሚገኙ ካምባሶች ቅበላ እየተካሄደ ሲሆን በሁለት ቀን ምዝገባው ተጠናቆ መማር ማስተማር ስራው እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

ተማሪዎችን የቱሉ አውሊያና የመካነሰላም ከተማ ነዋሪዎችና በጎ ፍቃደኞች ጭምር አቀባበል እያደረጉላቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ የመጣችው ተማሪ መቅደስ ታደሰ በሰጠችው አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ከማህበረሰቡ ጋር በወሎ የእንግዳ አቀባበል ባህል መሰረት መቀበሉ ባይተዋር እንዳንሆን የሚያደርግ ነው።

ይህም አካበቢውን ፈጥኖ ለመላመድ ከማገዙም ባለፈ ያለ ስጋት ትምህርታችን ላይ ብቻ እንድናተኩር እድል ይፈጥርልናል ብላለች።

የሀገራችንን ሰላም ለማይፈልጉ አካላት የፖለቲካ አጀንዳ መሳሪያ እንዳልሆን በቤተሰብ ተመክራ መምጣቷን ተናግራለች።

ተማሪ መቅደስ አክላም ዓላማዋ ላይ ብቻ አትኩራ ሀገሯንና  ህብረተሰቡን በምትችለው ሁሉ ለማገልገል ጠንክራ እንንደምትማር ገልጻለች።

መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከ6 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡