በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን የመጣንበትን ዓላማ ለማሳካት ከአደናቃፊ ሁኔታዎች በመራቅ ጠንክረን እንማራለን - አዲስ ገቢ ተማሪዎች

108

አምቦ፤ ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ) በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው አላስፈላጊ ከሆኑ አጀንዳዎች በመራቅ የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ጠንክረው እንደሚማሩ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተመደቡ 4ሺህ 200 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ሀጫሉ ካምፓስ እየተቀበለ ነው።

ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ነባር ተማሪዎች የተደረገላቸውን አቀባበል ከጠበቁት በላይ መሆኑንና እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀለችው ተማሪ ዘሪቱ ታደለ በሰጠችው አስተያየት አዲስ ገቢ ተማሪዎች ብዙ እንደሚቸገሩና ግራ እንደሚጋቡ ቢነገራትም የተደረገላት መልካም አቀባበል ስጋቷን እንደቀረፈላት ተናግራለች፡፡

"ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጣሁበትን ዓላማ ለማሳካት ጠንክሬ በመስራት ከራሴ አልፎ ለሀገሬ የምጠቅም የተማረ ዜጋ ለመሆኑ ጠንክሬ እሰራለሁ" ስትል ተናግራለች።

በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተደረገለት አቀባበል እንዳስደሰተውና "አምቦ የፍቅር ከተማ መሆኗን ያየሁበት ነው" ያለው ደግሞ ከምስራቅ ሸዋ ዞን አዲስ ገቢ ተማሪ ደስሉ ደርሱ ነው።

በቆይታው የመጣበትን ዓላማ ከሚያደናቅፉና አላስፈላጊ አጀንዳዎች በመራቅ በትምህርቱ ስኬታማ ለመሆኑ እንደሚሰራ አስታውቋል።

ከጎንደር ከተማ አዲስ ገቢ የሆነው ተማሪ አምባቸው ትልቅሰው እንደገለጸው ወደ ተቋሙ የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት ከማንኛውም አደናቃፊ ሁኔታዎች እራሱን እንደሚጠብቅ ተናግሯል፡፡

"በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን ጠንክሮ ተምሮ ለስኬት ከመብቃት ውጪ ሌላ አጀንዳ ሊኖረን አይገባም" የሚለው ተማሪ አምባቸው ለመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊነት የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቅል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች አዲስ አበባ ድረስ ትራንስፖርት መድቦ በማጓጓዝ ሊጋጥማቸው ከሚችል እንግልትና ወጪ ነጻ እንዳደረጋቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ  ተናግረዋል፡፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶክተር ብዙነሽ ሚደክሳ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው አዲስ የተመደቡ 4ሺህ 200  ተማሪዎችን በመቀበል ላይ ነው፡፡  

"ተማሪዎች በቆይታችሁ የመጡበትን  ዓላማ ለማሳካት በርትታው በመስራት የቤተሰቦቻቸውን ድካምና የራሳቸውን የወደፊት እቅድ ለማሳካት የሚያስፈልጋቸውን እውቀት መሸመት ላይ ማተኮር አለባቸው" ብለዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ አብዱረዛቅ ይሳቅ በበኩሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልፆ ህብረቱ ከነባር ተማሪዎች ጋር በመቀናጀት ለተማሪዎቹ ቤተሰባዊ አቀባበል እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም