አርቲስት ተስፋዬ ሲማ ዳያስፖራው ኤችአር6600 እና ኤስ3199 ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ የሚያደርገውን ትግል በስልትና በጥበብ ታግዞ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ

277

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማገዝ ገንዘብ በማሰባሰብ የሚታወቀው ኑሮውን በባሕር ማዶ ያደረገው አርቲስት ተስፋዬ ሲማ ዳያስፖራው ኤችአር6600 እና ኤስ3199 ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ የሚያደርገውን ትግል በስልትና በጥበብ ታግዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ።

አርቲስት ተስፋዬ ሲማ በአካል እና በበይነ-መረብ መርሐ ጥበባዊና ታሪካዊ ዝግጅት በማቅረብና ዳያስፖራውን በማስተባበር ገንዘብ አሰባስቦ በመለገስ ለአገሩ ይታወቃል።

አርቲስቱ በሕዳሴ ግድብ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሕግ ማስከበር ዘመቻው አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለአገርና ወገኑ ደራሽ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

በጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖቹን ለማገዝ በድምሩ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማሰባሰብ መለገስ ችሏል።

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው አርቲስት ተስፋዬ፤ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤቷ ኢትዮጵያ በቅርብ ከተፈጠሩ አገሮች አንጻር ያለችበትን ሁኔታ በማሰብ ዘወትር እንደሚቆጭ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።

አገሩን ከድኅነት ለማውጣትም በተለያዩ ዘመናት ወደ ውጭ የሄዱ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ- ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ለመደገፍ መነሳቱን ያወሳል።

በዚህ ዓላማ የተሰባሰበውን ገንዘብ በመላክ የተቸገሩ ኢትዮጵያዊያን ሲደሰቱ በማየቱ ደስታው ወደር እንደሌለውም ተናግሯል።

በኢትዮጵያ ላይ ሁለንተናዊ ጫና ለማድረግ የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ገልጾ፤ ይህን ተገቢ ያልሆነ ጫናና ጣልቃገብነት ለማስቆም በውጭ ያሉ አገር ወዳዶች በትጋት እየሰሩ እንደሆነ ያብራራል።

በአገረ አሜሪካ ኢትዮጵያን አብዝተው የሚወዱ፣ እጅግ የተማሩና ባለጸጋ የሆኑ ልጆቿ ኤችአር6600 እና ኤስ3199 ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ እየታገሉ መሆኑን ገልጿል።

ረቂቅ ህጎቹ በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችም የሚጎዱበት በመሆኑ የተቀናጀ ትግል ማድረግ እንደሚገባ አመልክቷል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያን ማገዝና መርዳት የሚሻ ከሆነ ክስተቶችን ተከትሎ በጊዜያዊነት ብቻ ሳይሆን በቋሚነት መደገፍ እንደሚገባው ገልጾ፤ በተለይ ረቂቅ ህጎቹ እንዳይጸድቁ በጋራ መቆም እንደሚገባ ጠቁሟል።

የትግል ስልቱም በጥበብና በዲፕሎማሲ እንጂ በስሜት መመራት እንደሌለበት ነው የተናገረው።

“ኢትዮጵያ ዴሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት አገር ሆና መገንባት አለባት” የሚለው ተስፋዬ ሲማ፤ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየሥራ ድርሻው አገሩን ማገልገል አለበት ባይ ነው።

በውጭ ዓለም ቆይታውም ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አገሩ እንድታሸንፍ እንደሚሰራ አረጋግጧል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም