የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት ከሚያመነጨው ገቢ ግብርን በአግባቡ ለመሰብሰብ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት ሊጠናከር ይገባል

132

ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከሚያመነጨው ገቢ ግብርን በአግባቡ ለመሰብሰብ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓትን ለማጠናከር በልዩ ትኩረት መሥራት እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባው የገቢዎች ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የአሥር ወራት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የገቢዎች ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው በገቢ አሰባሰብ፣ በኦዲት፣ በታክስና ቀረጥ የሕግ ተገዥነት፣ በንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ፣ በጋራ ገቢ አሰባሰብና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርበዋል።

ባለፉት አሥር ወራት ከአገር ውስጥ ገቢና ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ በአጠቃላይ 303 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 282 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።  

የተሰበሰበው ገቢ የእቅዱን 93 በመቶ ያሳካ ሲሆን ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ44 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

በአዲሱ የጋራ ገቢዎች የማከፋፈያ ቀመር መሰረት በ2014 በጀት ዓመት አሥር ወራት 26 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ከጋራ ገቢዎች የክልሎችን ድርሻ መተላለፉን ገልጸዋል።

በአሥር ወራት በአጠቃላይ 6 ሺህ 9 ድርጅቶችን የታክስ ኦዲት በማድረግ 40 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ የሚያስችል ውጤት ማግኘት መቻሉንም ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላት የገቢዎች ሚኒስቴር በ2014 በጀት ዓመት አሥር ወራት ከእቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ አበረታች መሆኑን አንስተዋል።

ምጣኔ ሃብቱ ከሚያመነጨው አንጻር ገቢ ለመሰብሰብ በግብር ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ የተወሳሰቡ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል አሰራር በመዘርጋት በኩል ተቋሙ እያከናወነ ያለውን ተግባር ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ህግና ሥርዓትን አክብረው ገቢን የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ቢኖሩም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የአገርና የሕዝብን ሃብት በማሸሽና በመሰወር፣ ሃሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀም፣ በሙስና ገቢን እያሳጡ ያሉ መኖራቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም የገቢዎች ሚኒስቴር በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አከፋፈል ሥርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ መሰረተ-ልማቱን የማልማት ጉዳይ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ፤ የእቅድ ክንውኑን እና የግብር ከፋዮችን አቅም ለማሳደግ እያከናወነ ያለውን ተግባር በጥንካሬ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከሚያመነጨው ገቢ ግብርን በአግባቡ ለመሰብሰብ ለኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት መጠናከር በልዩ ትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2014 በጀት ዓመት  የታክስ ፖሊሲና አስተዳደር ማሻሻያዎችንና የኢኮኖሚ እድገቱን ትንበያ ታሳቢ በማድረግ 360 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ ይዟል።

ሚኒስቴሩ ከምክር ቤት አባላት የተሰጠውን ምክረ-ሃሳብ በማከል ለተሻለ ውጤት የሚሰራ መሆኑን የተቋሙ ኃላፊዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም