በኮምቦልቻ ከተማ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በላይ የሚገነባው የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ሥራ ተጀመረ

96

ደሴ፣ ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ) በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በ806 ሚሊዮን ብር በጀት የሚገነባው የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ሥራ መጀመሩን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐመድ አሚን እንደገለጹት መንገዱ ተጠናቆ  ለአገልግሎት ሲበቃ በከተማው በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የትራፊክ መጨናነቅ ለማቃለል የሚያግዝ ነው።

የመንገዱ መገንባት የትራፊክ መጨናነቅን ከማቃለሉም ባለፈ የኢንዱስትሪ ከተማ እየሆነች ለመጣችው ኮምቦልቻ የበለጠ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

መንገዱ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ካምፓስ ጀምሮ በኢንዱስትሪ መንደሩ በኩል በአማር ፒፒ ፋብሪካ አድርጎ ዋናው መንገድ ጋር የሚገናኝ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

የተጀመረው አስፋልት መንገድ 7 ነጥብ 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ግንባታው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስታውቀዋል።

የመንገዱ ግንባታ ወጭ በፌደራል መንግሥት የሚሸፈን መሆኑን ገልፀው፤ ግንባታው በተያዘለት ጊዜና ጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር መንገድ ባለስልጣን ዋና ስራ አስክያጅ ወይዘሮ መዲና አቢ በበኩላቸው የአስፋልት መንገዱ የከተማውን ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው።

የመንገዱ ግንባታ ዮን አብ የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት የሚያከናውነው ሲሆን የመንገዱ የጎን ስፋት 21 ሜትር እንደሆነ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የመንገድ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኮምቦልቻ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢንዱስትሪ ከተማ እየሆነች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ ይህነኑ የሚመጥን መሰረተ ልማት እየተገነባ እንደሆነም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም