መንግሥት ክልሎች የሚፈጥሩትን ቀጠናዊ የመልካም ግንኙነት ተግባራት ይደግፋል-ሰላም ሚኒስቴር

108

ሚዛን አማን፣ ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ) እንደ ሀገር ከሚደረጉ ጠንካራ ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነቶች ጎን ለጎን ክልሎች የሚፈጥሩትን ቀጠናዊ የመልካም ግንኙነት ተግባራት የፌዴራል መንግሥት እንደሚደግፍ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሰላም ሚኒስቴር በሚዛን አማን ከተማ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ሀገር አቀፍ የሰላምና ፀጥታ ተቋማት የጋራ የምክክር መድረክ  ዛሬ አጠናቋል።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት  ኢትዮጵያን  የሚዋሰኑ የምስራቅ አፍሪካ  ሀገሮች የርሃብ፣  የእርስ በርስ  ግጭትና  የዓባይ  ወንዝን  መሠረት ያደረጉ ችግሮችን  እያስተናገዱ ይገኛሉ።

በመሆኑም ይህንን ችግር ለማቃለል በቀጠናው የሚኖሩ ህዝቦችን መሠረት ያደረገ የሰላም ግንባታ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የሀገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለጎረቤት ሀገሮች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ያማከለ መልካም ግንኙነት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ለመፈጠር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በተለይ በሱዳን አዋሳኝ አካበቢ ከድንበር ጋር የተያዘውን ችግር በዲፕሎማሲያዊ ሥርዓት በሰላም ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት ይሰራል ብለዋል።

ይህ ስራ እንዲጠናከር ሁሉም ክልሎች ከጎረቤት ሀገሮች አዋሳኝ መዋቅሮች ጋር በመነጋገር ቀጠናዊ ድንበር ተሻጋሪ  ወንጀሎችን  ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እንደ ሀገር ከሚደረጉ ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነቶች በተጨማሪ ክልሎች የሚፈጥሩትን ቀጠናዊ የመልካም ግንኙነት ተግባር የፌዴራል መንግሥት እንደሚደግፍም አስታውቀዋል።

ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ከሚዋሰኑ ክልሎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን ነው።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ  ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በምዕራብ ኦሞ ዞን በኩል ድንበር እያለፉ በአርብቶ  አደሩ አካባቢ ከብት  የመዝረፍ    ሁኔታ አልፎ አልፎ  እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ችግሩን ለመፍታት  በፌደራል  መንግሥት  የሚመራ   የውይይት መድረክ  ለማዘጋጀት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ በፀጥታ አካላት ጭምር የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የመሳሪያ ዝውውር በድንበር አካባቢ እንደሚበራከት የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊው ናቸው።

እንደ ሀገር ከሚፈጠረው ግንኙነት ባሻገር ታችኛው መዋቅር ተናቦ ሰላም እንዲከብር እየሰራ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።