በድሬዳዋ የኅብረተሰቡን የማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

97

ድሬዳዋ/ኢዜአ/ ግንቦት 11/2014 በድሬዳዋ ከተማ የኅብረተሰቡን የማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ተግባራትን ከዳር ለማድረስ አመራሩ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።

ቋሚ ኮሚቴ በድሬዳዋ ከተማ በዓለም ባንክ   ብድርና   በአስተዳደሩ  በጀት እየተገነቡ  የሚገኙ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ፕሮጀክቶችን የሥራ አፈጻጸም  ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

ቋሚ ኮሚቴው ጎርፋን ለመከላከል፣ በልማታዊ ሴፍትኔት የደሃ ደሃዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን፣ የአስፋልትና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታዎችን ተመልክቷል።

እንዲሁም  የዘመናዊ  ቄራ ፕሮጀክቶችንና  በከተማ በብዙ ሚሊዮን ብር በጀት እየተገነቡ የሚገኙ ትላልቅ ድልድዮችንና የጎርፍ  መከላከያ ግንቦችን  የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጎብኝቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ለሁለት ቀናት ያካሄዱትን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ በተሰሩት ተግባራትና ክፍተቶች ላይ ከአስተዳደሩ  ከንቲባ  ከድር  ጁሃርና ከአስተዳደሩ  አመራሮች ጋር መክረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ዋለ በውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ የልማት ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ የሚያቃልሉ ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም በአብዛኛው በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙና የህብረተሰቡን ተሣትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ከተማዋን ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የተሰሩ ግንቦች፣ ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶችና ድልድዮች አበረታችና በአርዓያነት የሚጠቀሱ  መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በተጨማሪም በከተማው የሚገኙ የደሃ ደሃ ነዋሪዎችን በከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር በማሳተፍ ኑሯቸውን እንዲቀየር የማድረጉ ሥራ አበረታች በመሆኑ  ተጠናክሮ  መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ አቶ ተሾመ ገለፃ አመራሩ እነዚህን አበረታች ሥራዎች በማጠናከር ፕሮጀክቶቹን ዳር ለማድረስ  ርብርቡን ማጠናከር አለበት።

በተለይ የአስፋልት መንገዶች ግንባታ መጓተት፣ የጎርፍ ማስወገጃ ቦዮችን የማጽዳት ፣ ተገንብቶ ለተጠናቀቀው ዘመናዊ ቄራ  የውሃና የወሰን ማስከበር ችግሮች የመፍታት፣ የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም የተጠናቀቁና እየተገነቡ የሚገኙ ቤቶችን ዳር ማድረስ ለህብረተሰቡ የማከፋፈል ሥራን ማፋጠን እንደሚገባ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ቋሚ ኮሚቴው ድሬዳዋ ተገኝቶ ያካሄደው የመስክ ግምገማ የበለጠ ለመስራት የሚያነሳሳና የሚመሰገን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከንቲባ ከድር አክለውም በዘጠኝ ወራት  የሥራ አፈጻጸም  ግምገማ  ወቅት  የተፈጠሩ ክፍተቶች ተለይተው ለመፍትሄዎቻቸው ርብርብ  እየተደረገ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሚፈለገው መጠን ለመፍታት እንቅፋት የሆነበት የበጀት ችግር ቢሆንም ባለው ውስን በጀት ፣ ጉልበት፣ እውቀት ህብረተሰቡን ከጎኑ አሰልፎ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተረባረብ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም