በሀዋሳ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የእግር ጉዞ ሊካሄድ ነው

158

ሀዋሳ፤ ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት “ ለአረጋዊያን ክብር እንጓዛለን ” በሚል መሪ ሀሳብ የእግር ጉዞ የፊታችን እሁድ እንደሚካሄድ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ አስታወቀ።

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የእግር ጉዞውን አስመክቶ መግለጫ በሰጠበት ወቅት የድረጅቱ የሀዋሳ ቢሮ ማርኬቲንግ ኦፊሰር ወይዘሮ ሕይወት መለሰ እንደገለፁት የፊታችን እሁድ ግንቦት 14/2014 ዓም ከንጋቱ 12 ሰአት ከ30 ጀምሮ 10 ሺህ ሰዎች የሚታደሙበት የእግር ጉዞ ይካሄዳል።

የእግር ጉዞው መነሻውና መድረሻውን በሀዋሳ ሱሙዳ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው እንደሚያደርግና አራት ኪሎ ሜትር ያህል እንደሚሸፍንም ጠቁመዋል።

በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የሀዋሳ ቢሮ ኃላፊ አቶ እስክንድር ሽመልስ የእግር ጉዞው ዓላማ ገቢ ከማሰባሰብ ባሻገር ስለ አረጋውያን ክብርና ሊደረግላቸው ስለሚገባ እንክብካቤ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ እስክንድር ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በ23 ዓመታት ቆይታው ከ150 ሺህ በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ያደረገ የድጋፍ ሥራዎች መስራቱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሀዋሳ ከተማ ባለው ሁለገብ የአረጋዊያን ማዕከል ውስጥ 120 አረጋዊያን ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን ቤት ለቤት በሚሰጠው የድጋፍ አገልግሎት ደግሞ 150 አረጋዊያንና 100 ሕፃናት ተካተዋል።

በቀጣይም በማዕከሉ አገልግሎት የሚያገኙ አረጋዊያንን ቁጥር ወደ 200 ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ታዋቂ አርቲስቶች፣ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች፣የሜሪጆይ ኢትዮጵያ የበላይ አመራሮች፣ የመንግስት የሥራ ኃፊዎች፣ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አመላክተዋል።