የሀረሪ ክልል ለከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ከ234 ሚሊዮን ብር በላይ የበጀት ክለሳ እቅድ ፀደቀ

88

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ለከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም 234 ሚሊየን 693 ሺህ 902 ብር የበጀት ክለሳ እቅድ አፀደቀ።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የዘጠኝ ወራት ስራ አፈፃፀምን ገምግሟል፡፡

የበጀት ክለሳው ያስፈለገው ተጨማሪ በጀት የጠየቁ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው መሆኑ ተገልጿል።

በወቅቱም የክልሉ የከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፈቲ ረመዳን የተቋሙን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።

ስራ አስኪያጁ በሪፖርቱ እንደገለፁት በበጀት አመቱ ለማከናወን ከታቀደው 41 ፕሮጀክቶች 26ቱ ስራቸው የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪዎቹ 15 ፕሮጀክቶች ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው።

በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ “የከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ የህዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ አበርክቶ ያለው በመሆኑን በአግባቡ መጠቀም ይገባል” ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አበረታች አፈፃፀም ያስመዘገቡ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በማመላከት ዝቅተኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ግዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንዲደረግም አሳስበዋል።

ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን በግዜ አጠናቆ ወደ ስራ ማስገባት እንደሚያስፈልግም ርእሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ለማከናወን በጀት ወስደው የተሰወሩ ማህበራትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ሊሰራ እንደሚገባና አላስፈላጊ የሆኑ ወጪዎችን በማስቀረት የተስተዋሉ ጉድለቶችም ሊስተካከሉ እንደሚገባ አቶ ኦርዲን በድሪ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም