በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የተጀመረው የቅንጅት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

79

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የተጀመረው የቅንጅት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በኦሮሚያ ተዘግተው ከተከፈቱ ኢንዱስትሪዎች መካከል የተወሰኑትን ጎብኝተዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ለማስቻል "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል ንቅናቄ መጀመሩ ይታወቃል።

በንቅናቄው በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው ከቆዩ 400 በላይ ኢንዱስትሪዎች 118ቱ ወደ ሥራ መግባታቸው ተገልጿል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ጉብኝት፤ የኢንዱስትሪ ኃላፊዎች በግብዓት፣ በብድር አቅርቦትና በሌሎች ምክንያቶች ተዘግተው እንደቆዩና በተደረገላቸው ድጋፍ ዳግም ወደ ሥራ መግባታቸው ገልጸዋል።  

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ታመነ እንዳሉት በንቅናቄው የተዘጉ ኢንዱስትሪዎችን ሥራ ለማስጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ማነቆዎችን በጋራ ለመፍታት  ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።  

በንቅንቄው በተሰራው ሥራ የተለያዩ ለውጦች መጥተዋል ያሉት ኃላፊዋ 118 ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪ በሚዘጋበት ወቅት በርካቶችን ሥራ አጥ በማድረግ በግለሰቦች ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ ባለፈ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ኪሳራን ያደርሳል።

ስለሆነም ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ የአሰራር ክፍተት፣ የግብዓት እጥረትና የውጭ ምንዛሬ ችግር እንዲፈታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሰራቱን አንስተዋል።

በቀጣይም ለመዋቅራዊ ሽግግሩ ትልቅ ፋይዳ ያለው የአምራች ዘርፉ አስተዋፆውን እንዲወጣ የሚደረጉ ድጋፎች የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው በንቅናቄው በክልሉ ማምረት ያቆሙ 139 ኢንዱስትሪዎች መለየታቸውን ገልፀዋል።

የጥሬ እቃዎች አቅርቦት እጥረት፣ መሰረተ-ልማት፣ የባንክ ብድር ያለመመለስና ከመሬት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን በንቅናቄው መለየቱን አክለዋል።

ክልል አቀፍ መድረክ በማዘጋጀት የዘርፉ ችግሮች ተለይተው በክልሉ አቅም ለመፍታት ጥረት መደረጉንና በክልሉ አቅም መፈታት የማይችሉት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም