“ከአገርና ሕዝብ ጠላቶች ጋር እየተዋጋንም የልማትና ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን”

90

ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ)  ከአገርና ሕዝብ ጠላቶች ጋር እየተዋጋንም የልማትና ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ።

የመከላከያ ፋውንዴሽን ያስገነባቸውን 529 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለሰራዊቱ አባላትና ሲቪል ሰራተኞቹ በዕጣ አስተላልፏል፡፡  

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በአዲስ አበባ ሰሚት ቁጥር 2 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገነቡ ባለ 7 እና 9 ወለል ህንጻዎች ሲሆኑ ግንባታቸው የተጠናቀቀ እና መሠረተ-ልማት የተሟላላቸው ናቸው።

በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው የተጠናቀቁትን ቤቶች በወጣላቸው ዕጣ መሰረት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ለዕድለኞቹ አስረክበዋል።

ዶክተር አብርሃም በመርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት “ከአገርና ሕዝብ ጠላቶች ጋር እየተዋጋን፣ እያለማንና  እየገነባን መሆኑን የቤቶቹ ግንባታ እውን መሆን አንዱ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላም የአገርን ክብርና ሉዓላዊነት እያስጠበቅን የሰራዊቱን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተያዙ ዕቅዶችን እናሳካለን ሲሉ ተናግረዋል።

ፋውንዴሽኑ ሌሎች በርካታ ቤቶችን በመገንባት ላይ ቢሆንም አሁንም ፍላጎቱን ከአቅርቦቱ ጋር ለማጣጣም አዳዲስ አሰራሮች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

ለዚህም የሰራዊቱን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚረዱ አዳዲስ ዕቅዶችን በማውጣት በሕግ እንዲደገፉ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።

የመከላከያ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሜጀር ጄነራል ኩምሳ ሻንቆ፤ ፋውንዴሽኑ ከቤት ግንባታ ባሻገር የሰራዊቱን ዝግጁነት የሚያሳድጉ ሌሎች ተግባራትንም በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።  

በዕጣው የቤት ባለቤት የሆኑ የሰራዊቱ አባላት ባገኙት እድል መደሰታቸውን ገልጸው፤ ለበለጠ ግዳጅና ኃላፊነት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በአገሪቷ ካሉ የግንባታ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ሲሆን ባለፉት ጊዜያት የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ እና የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የግንባታ ሥራዎችን አከናውኗል።