ምክር ቤቱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ መራ

417

ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ)  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ መራ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

የምክር ቤቱም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ረቂቅ አዋጁን የተመለከተ አጭር መግለጫ ያቀረቡት በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፤ ረቂቅ አዋጁ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመጋቢት ወር በዝርዝር አይቶ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱን አስታውሰዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የተቀመጠውን የሪፎርም አቅጣጫ ለማሳካት ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸው፤ ተቋሙ ተልዕኮውን በብቃት መወጣት እንዲችል የአዋጅ ማሻሻያ መቅረቡን ተናግረዋል።

“በአገሪቱ ላይ የሚፈጸመውን ጦርነት የመመከት ሂደት በአግባቡ ካልተመራ ብሔራዊ ደህንነትና ጥቅምን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል በመሆኑ የሚቃጣውን የስነ ልቦና ጦርነትን ለመመከት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ተግባራትን በበላይነት የሚመራና የሚያስተባብር ተቋም እንዲሆን በማስፈለጉ እነዚህን ተግባራት የሚያመላክት ድንጋጌ  እንዲካተት ተደርጓል” ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በረቂቁ ላይ አስተያየት ከሰጡ በኋላ ለዝርዝር እይታ ረቂቅ አዋጅ 7/2014 ሆኖ በዋናነት ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በተባባሪነት ደግሞ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች በሙሉ ድምጽ ተመርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም