ለፀጥታ ችግር መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ በመፍታት አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ይሰራል - አቶ ብናልፍ አንዷለም

228

ሚዛን አማን፣ ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ለፀጥታ መደፍረስ መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ በመፍታት አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

ሚኒስቴሩ በሚዛን አማን ከተማ እያካሄደ ባለው የምክክር መድረክ የዘጠኝ ወራት የሰላምና ፀጥታ ተግባራትን በመገምገም በቀጣይ ትኩረት የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች ላይ  አቅጣጫ አስቀምጧል።

ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ባለፉት ሦስት ወራት በተሰሩ ስራዎች በአብዛኛው ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም መታየቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን ከመዋቅራዊ አሰራር ጎን ለጎን ተጨማሪ የጸጥታ ማስከበር ተግባራት ማከናወን እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

በቅደመ ግጭት አፈታት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው "አሁን እየተፈጠረ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በሁሉም አካባቢዎች እንዲኖር ማድረግና ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ለዚህም ለፀጥታ ችግር መከሰት ምክንያት የሚሆኑ ሁኔታዎችን በመለየት እንዲፈቱ መስራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቀጣይ የሥራ አቅጣጫ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ሀገር የጋራ የሆኑና በአካባቢ የሚለያዩ የግጭት መንስኤዎችን ባህሪ በመረዳት መፍትሄ ለማምጣት መሰራት ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።

"የህግ የበላይነት ባልተከበረበት እና ፍትሃዊነት ባልሰፈነበት ሀገር ስለ ሰላም ማውራት ድካም በመሆኑ ህግን የማስከበር ተግባር በሁለም አካባቢ መፈጸም አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ህግን የማስከበር ሥራ ክልሎች የጀመሩትን በቅንጅት የመስራት ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።

"የክልሎች የእርስ በእርስ ግንኙነት ከአመራሩ ባለፈ በህዝብ ትስስር እንዲጠናከር በአዋሳኝ አካባቢዎች ምቹ ሁኔታን ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በበኩላቸው ወሰን ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ተናቦ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ለጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በሚሆኑ ችግሮች ላይ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ግጭት ይከሰትባቸው የነበሩ አካባቢዎች ወደ አንጻራዊ ሰላም መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

"አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን ሙሉ በሙሉ የማስቆም ደረጃ ላይ ለመድረስ ህብረተሰብን ያሳተፈ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊው እንዳሉት ክልሉን ከጸረ ሰላም ኃይሎች በመጠበቅ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የፀጥታ አስከባሪ አካላትን በማሰልጠን ስጋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች  የማሰማራት ስራ እየተሰራ ነው።

"በአሸባሪው ሸኔና የሙሩሌ ታጣቂዎች የሚፈጸመውን ወሰን ተሻጋሪ ጥቃት ለመከላከል ከአጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም