ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት 2 ሺህ 400 መጻሕፍት አበረከተ

163

ግንቦት 10/2014 /ኢዜአ/ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከሠራተኞችና ከጣቢያው ከአድማጭ ተመልካቾች ያሰበሰባቸውን 2 ሺህ 400 መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበረከተ።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት "ሚሊዮን መጻህፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ" በሚል መሪ ኃሳብ ለአንድ ወር መጻሕፍትን ለማሰባሰብ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ እየሰጡ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሰራተኞችና ከጣቢያው አድማጭ ተመልካቾች ያሰባሰባቸውን 2 ሺህ 400 መጻህፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በዛሬው ዕለት አስረክቧል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው መጻህፍቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ወክለው ለመጡት ዶክተር ታምራት ኃይሌ አስረክበዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ያስረከባቸው መጽሃፍት በሳይንሰ፣ ጥበብና በአገር ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውም ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ዙር የመጻሕፍት ማሰባሰብ ሂደትም ከቁጥር ይልቅ ለይዘት ትኩረት መስጠታቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

መጻህፍቱ የተለያየ ስብጥር ያላቸውና የዓለምን ሁለንተናዊ ተሞክሮ የሚያሳዩ መሆናቸውን እንዲሁ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለአብሮሆት ቤተ-መጻሕፍት ያደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ መሆኑን ገልጸው ተቋሙ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በርክክብ መርኃ ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ወክለው የተገኙት ዶክተር ታምራት ኃይሌ በበኩላቸው፤ ልገሳው ምክንያታዊና መረጃ ያለው ትውልድ ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።

በዚህም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ይዘት ላይ ትኩረት ያደረጉና ትውልዱን የሚገነቡ መጻሕፍት   በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አገርና ትውልድን ለመገንባት ይረዳ ዘንድ በቀጣይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ሁለገቡ የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን መጻህፍት የማሰባሰብ ሥራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ቤተ-መጽሐፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻህፍት የመያዝ አቅም አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም