የሐረሪ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በፍራፍሬ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ ይከናወናል

213

ሐረር፤ ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ)፡ በሐረሪ ክልል የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የክልሉን የፍራፍሬ ምርታማነት ለማሳደግ  ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ሚስራ አብደላ ገለጹ።

ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ለኢዜአ እንደገጹት በክልሉ በዚህ ዓመት ከሚተከሉት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት የፍራፍሬ ችግኞች ይሆናሉ።

የአካባቢውን አርሶ አደር ፍላጎት መሰረት በማድረግ ለፍራፍሬ ልማት ትኩረት መሰጠቱን አመልክተው፤100 ሺህ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎች መዳቀላቸውን በማሳያነት አንስተዋል።

ችግኞቹ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር በገቢ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉት አስረድተዋል።

እንደ ወይዘሮ ሚስራ ገለጻ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ የአካባቢን የአየር ሁኔታ የሚያሻሽልና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጥምር ደንና ለባህላዊ መድሃኒትነት የሚያገለግሉ ችግኞች ይተከላሉ።

 ክልሉ የሚታወቅበት የሐረር ቡና ልማትን ማጠናከር የሚያስችል  የቡና ችግኝ የማፍላቱ ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የኤረር ቂሌ ችግኝ ጣቢያ ሃላፊ አቶ ዘሪሁን አያሌው በበኩላቸው በችግኝ ጣቢያው ከ800 ሺህ በላይ የፍራፍሬና ሌሎች ችግኞች  መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በጣቢያው ከተዘጋጁት መካከል 70 በመቶው ፍራፍሬ መሆናቸውን አመልክተው፣የተዳቀሉ የአቮካዶና የማንጎ ዝርያዎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

 የችግኝ ጣቢያው ሰራተኛ አርሶ አደር ፋጡማ ሙመድ በበኩላቸው ''ከማከናውነው የእርሻ ስራ ጎን ለጎን እዚህ ችግኝ ጣቢያ ተቀጥሬ ችግኝ በማፍላት ገንዘብ እያገኘሁና እየተጠቀምኩኝ ነው'' ብለዋል።

በሐረሪ ክልል ባለፉት ሶስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተተከሉት ሰባት ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 73 በመቶው መጽደቃቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም