ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሴክተር ሚና ወሳኝ ነው - ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ

202

አርባምንጭ ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ) ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሴክተር ሚና ወሳኝ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ገለጹ፡፡

አገራችን የሚትከተለው ሁሉ አቀፍ የዕድገት ሞዴል ውስጥ ኢንዱስትሪ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ቀልጣፋ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ይገባል።

ይህ ደግሞ "ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ከባቢን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና አለው" ያሉት ሃላፊው፤ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሴክተር ደግሞ የሰራተኛና አሳሪ ትስስሩን በተገቢው መወጣት አለበት ብለዋል።

ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ከተሰጠው ትኩረት አንጻር በዘርፉ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ባለሙያዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የስራ ስምሪት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ለአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መገኘቱን ያነሱት ዶክተር ዲላሞ፤ ያንን ተደራሽ የሚያደርግ ቀልጣፋ የስራ ስምሪት   መፈጠር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ለኢንዱስትሪው ሰላም የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ሚና መጎልበት እንዳለበት ያመላከቱት ሃላፊው፤ ዘርፉ ይህንን ሚናውን እንዲወጣም ያለው የህግ ማዕቀፍና አፈጻጸሙ በተግባር ሊረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።

የደቡብ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኦንጋዬ ኦዶ በበኩላቸው የአሠሪና ሠራተኛ መብቶች እንዲከበሩና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን ቢሮው በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመከላከል በተደረገ ጥረት አበረታች ለውጥ መምጣቱን የጠቆሙት ሃላፊው፤ ከችግሩ ውስብስብነት አንፃር ግን ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ አስታውቀዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ህግና አዋጅ ማዕቀፎች፣ በአፈጻጸም ተግዳሮትና መፍትሄዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

እንዲሁም በደቡብ ክልል የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከል በተደረጉ ጥረቶችና የተገኙ ውጤቶች፣ በህጋዊ የስራ ስምሪት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ምክክር ይደረጋል።

በኮንፈረንሱ ከክልል፣ ከዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የሴክተሩ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም