ለሰላም ዘብ በመቆም የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እየተወጣን ነው-የሐዋሳ ወጣቶች

156

ሀዋሳ፤ ግንቦት 10/2014 (ኢዜአ)፡ ለሰላም ዘብ በመቆም የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እየተወጣን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐዋሳ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

ከከተማዋ ወጣቶች መካከል  ቴዎድሮስ ደምሴ እንደገለጸው እሱና ጓደኞቹ በሚኖሩበት ሀዋሳ ከተማ የባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማ  ሰላምን የማስጠበቅ ስራ  እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል።

ሰላማዊ ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እያገዝን ነው ያለው ወጣቱ፤ ምሽት ላይ ሮንድ በመውጣት በአካባቢው ሰላም ማስጠበቅ ስራ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁሟል።

ወጣቱ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉት የገለጸው ወጣት ቴዎድሮስ፤ ''ጥያቄዎቻችንን መመለስ የምትችል ሀገር እንድትኖረን ለሰላምና ጸጥታ ስራ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብሏል።

በሀራዊ ጉዳዮች ላይ በየ15 ቀኑ ውይይት የማድረግ ልምድ በከተማው ወጣቶች ዘንድ መኖሩን አመላክቷል።

የተመቻቸላቸውን የሥራ እድል በመጠቀም የከተማ ግብርና እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጸው ወጣቱ፤ የተመቻቸውን የስራ እድል ለመጠቀም ሰላሟ የተረጋገጠች ሀገር መፍጠር እንደሚገባ ጠቁሟል።

 ወጣት እታገኝ ደምሴ በበኩሏ በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ የወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁማ፤ ከማህበራዊ የትስስር ገጽም ሆነ ከሌሎች የመረጃ ምንጮች የሚገኙ መረጃዎች የጸብ መንስኤ እንዳይሆኑ ትክክለኛነታቸውችን ማረጋገጥ ይገባል ብላለች።

"የሀገር ሰላም በወጣቱ እንደሚጠበቅ አምናለሁ" የምትለው ወጣቷ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከመንግስት አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ባልተረጋጋችና ሰላም በሌላት ሀገር የሚኖር ህዝብ ሁሌም የጉዳቱ ሰለባ መሆኑን ወጣቱ አምኖ ለሀገሩ ሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪዋን አስተላልፋለች።

ወጣቱ ያለበትን ሀገራዊ ሃላፊነት  አካባቢውን በመጠበቅ ማረጋገጥ እንዳለበት የተናገረው ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ወጣት ገበየሁ ገንታ ነው።

 የከተማዋን ወጣቶች በማስተባበር ጭምር በሰላምና ጸጥታ ስራ ላይ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የገለጸው ወጣት ገበየሁ፤ወጣቱ በመደራጀት አካባቢውን ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

ምክንያታዊና ሚዛናዊ በመሆንም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ሊያጠናክሩ በሚችሉ በጎ ተግባራት ላይ መሳተፍ ከሁሉም ወጣት  እንደሚጠበቅ ጠቁሟል።

 ጸጉረ ልውጥ የሆኑ ሰዎች ሲያጋጥሙ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት  ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጾ፤ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ መረጃዎች ተከትሎ በስሜት የሚጓዙ ወጣቶችን ሰብዕና ለመገንባት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁሟል።

ኃላፊነት በጎደለው መልኩ  አብሮ የመኖር ታሪክን ለማጥለሽት የሚደረግ ሙክራ ተቀባይነት እንደሌለው  ወጣቶቹ  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም