አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የኢትዮ-ሶማሊያ ግንኙነትን ይበልጥ እንደሚያሳድጉት ሙሉ እምነት አለኝ-ሶማሊያዊው ፕሮፌሰር ሶንኮር ጌየር

55

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ)አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ለረዥም ዘመናት የዘለቀውን የኢትዮ-ሶማሊያ ግንኙነትን ይበልጥ እንደሚያሳድጉት ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉ በሶማሊያ የፌዴራሊዝምና ደህንነት ትንተና ኢንስቲትዩት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ሶንኮር ጌየር ተናገሩ፡፡

የሶማሊያ ምክር ቤት ባለፈው ሰኞ ሀሰን ሼክ መሃሙድን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡ ይታወሳል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት በቀጣናው የተረጋጋ የፖለቲካ አውድ መኖር ሶማሊያንና ዓለምን ወደ ስምምነት የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሶንኮር ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ረዥም ዘመን የተሻገረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም የአገራቱ የጋራ ራዕይን መሰረት በማድረግ ወዳጅነታቸው ከዚህ በላቀ ደረጃ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አንጻር አዲስ የተመረጡት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ መሰረት በማድረግ ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩትም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያ በብዙ መስኮች ለሶማሊያ ጠቃሚ አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ አገራቱ በተለይ በሰላምና ደህንነት፣ንግድ እንዲሁም በልማት ዘርፎች ላይ በትብብር እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት፡፡

የአፍሪካ ቀንድ አገራት ለአካባቢው የጋራ ተጠቃሚነት እድል የሚፈጥር ፖሊሲ ሊኖራቸው እንደሚገባ የተናገሩት ፕሮፌሰር ሶንኮር፤ ከዚህ አኳያ አገራቱ ከፉክክር ይልቅ በትብብር ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ሊኖራቸው እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ አገራት በትብብር ከመሥራት ውጭ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸውም ነው ያነሱት፡፡

በቀጣናው ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ልማትን በማረጋገጥ የቀጣናውን ህዝቦች አኗኗር እንደሚያሻሽለው ገልጸው፤ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ያለንን የጋራ የልማት አጀንዳ የሚያስፈጽም ራዕይ ያለው አመራር ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡

ፕሮፌሰር ሶንኮር አዲሱ ፕሬዝዳንት በሶማሊያ የፖለቲካ እርቀ-ሰላም በማውረድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን እንደሚያሰፍኑም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

በሶማሊያ የተከናወነው ምርጫ በሰላም መጠናቀቁ ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ትልቅ ስኬት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አዲሱ ፕሬዝዳንት መሃሙድ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ባደረጉት ቅስቀሳ ከሶማሊያ ባለፈ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን እንደሚሰሩ መናገራቸውንም ፕሮፌሰር ሶንኮር አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ከፍ ያለ ዋጋ ከከፈሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ግንባር ቀደም መሆኗንም ፕሮፌሰሩ አስታውሰዋል፡፡