አሸባሪው ህወሓት የአገርን ክብር፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለመሸርሸር ያደረገው ጥረት ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ነው

60

ግንቦት 11/2014/ኢዜአ/  አሸባሪው ህወሓት የአገርን ክብር፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለመሸርሸር ያደረገው ጥረት ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ነው ሲሉ ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉ አንድ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ተናገሩ።

በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ደግሞ አሜሪካዊ የሆኑት ጌታቸው አማረ፤ አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ጥፋት እና ውድመት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በአፋር ክልል በነበራቸው ጉብኝትም የጉዳቱ ሰላባ ለሆኑ አካባቢዎች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን አሸባሪ ቡድኑ አስነዋሪ ተግባራትን በመፈጸም በማኅበረሰብ ላይ የከፋ በደልና ጥፋት ማድረሱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ክብር፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለመሸርሸር አሸባሪው ህወሓት ያደረገው ጥረት ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ሆኖም የአሸባሪውን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የፈጸሙት ገድልና ያስመዘገቡት ድል ደግሞ በደማቁ የሚጻፍ ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በውጭ ሀገራት አስፈፃሚዎቹ በኩል አሁንም የጥፋት አላማውን ለማሳካት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የጥፋት እቅዱ ለአገራቸው ዘብ በቆሙ ልጆቿ እና በመላው ዓለም በሚገኙ አገር ወዳድ  ወገኖች የሚሳካ አይሆንም ብለዋል።

በኢትዮጵያ እውን የሆነው ለውጥ በርካታ ተስፋዎችን ይዞ በመነሳት ብዙ የተጓዘ ቢሆንም በአሸባሪው ህወሃትና በአገር ጠሎች እኩይ አላማ ለውጡ በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ለውጡን ከዳር ለማድረስና ቀጣይ ፈተናዎችን በጋራ ለማሸነፍ በተለይም ዳያስፖራው ድጋፍና እገዛውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ቆንስላ ሰራተኞችና አገር ወክለው የተመደቡ አምባሳደሮች በዲፕሎማሲው መስክ ከምን ጊዜም በላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ከዲፕሎማቶችና ከዳያስፖራው ጥረት በተጨማሪ መንግስት ሌሎች ተጨማሪ ጥረቶችን በማድረግ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ መስራት ይጠይቃል ሲሉ አስገንዝበዋል።