አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፀጥታ ተቋማት ላይ የተከናወነው የሪፎርም ስራ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቦበታል

64

ግንቦት 11/2014/ኢዜአ/ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፀጥታ ተቋማት ላይ የተከናወነው የሪፎርም ስራ ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የመከላከያ ሠራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ገለፁ።

ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ይህን ያሉት የመከላከያ ዋር ኮሌጅ “የፀጥታ አካላት ለውጥና የሲቪል-ወታደራዊ ግንኙነት ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች” በሚል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ነው።

በውይይቱ ጀነራል መኮንኖች፣ የክልልና የፌደራል የፀጥታ አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የቀድሞ ጦር ሠራዊት አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን መድረኩ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ የፀጥታ አካላትን ከፖለቲካዊ አመላካከትና ወገንተኛነት ነጻ ያደረገ እና የአገርን ጥቅም ያስቀደመ የፀጥታ ተቋማት ሪፎርም መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የአገሪቱን ወቅታዊ የፀጥታና ደህንነት ስጋቶች ታሳቢ ያደረገ ጥልቅ የለውጥ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ በስልጠና እና አደረጃጀት የጸጥታ ተቋማት ጠንካራ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት።

ሌተናል ጀነራል ይመር አክለውም፤ ተቋማቱ ተልዕኳቸውን በአግባቡ ተረድተው አገርን ከየትኛውም ውጫዊና ውስጣዊ ችግር መታደጋቸውን ጠቅሰዋል።

በህግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻ ወቅት የተመዘገበው አመርቂ ድል በፀጥታ ተቋማቱ ላይ የተከናወነው የሪፎርም ስራ ስኬታማነትን በግልጽ እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ስኬታማ ተግባር ማከናወኗን የተናገሩት ሌቴናል ጀነራል ይልማ፤ በሪፎርሙም ይህን ስኬት ይበልጥ ከፍ የሚያደርጉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

ሁሉም የፀጥታ ተቋማት በቀጣይ ከፖለቲካዊ ወገንተኛነት ነፃ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የጥላቻ ትርክቶችን በማህበረሰቡ ውስጥ እየቆሰቆሱ ግጭት በመፍጠር አገር ለማተራመስ በሚሰሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

በመድረኩም የፀጥታ አካላት ለውጥና የሲቪል ወታደራዊ ግንኙነት፣ የዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያ ተሞክሮ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች፣ ወቅታዊ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎችን የሚመለከቱ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።