የመከላከያ ሚኒስቴር ፋውንዴሽን 529 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለሰራዊቱ አባላትና ሲቪል ሰራተኞቹ በዕጣ እያስተላለፈ ይገኛል

880

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ)የመከላከያ ሚኒስቴር ፋውንዴሽን በአዲስ አበባ ያስገነባቸውን 529 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለሰራዊቱ አባላትና ሲቪል ሰራተኞቹ በዕጣ እያስተላለፈ ይገኛል።

በዛሬው ዕለት ሰሚት ቁጥር 2 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመተላለፍ ላይ የሚገኙት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው የተጠናቀቀ እና የመሠረተ ልማት የተሟላላቸው ናቸው ተብሏል።

እየተካሄደ በሚገኘው መርሃ ግብር ላይም የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የሰራዊቱ አመራሮች፣ ከፍተኛ መኮንኖችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመታደም ላይ ይገኛሉ።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ከባለ አንድ እስከ ባለ አራት መኝታ ያላቸው ሲሆን ግንባታውንም የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ያከናወነው መሆኑም ተነግሯል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹም ባለ 7 እና 9 ወለል ህንጻ ሲሆኑ በዛሬው ዕለትም ለባለዕድለኞች በዕጣ እየተላለፉ ይገኛሉ።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በአገር ደረጃ ከ5ሺ 795 የሚሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዛሬው ዕለት የተላለፉት የመኖሪያ ቤቶችም የዚሁ አካል ሆነው ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ መሆናቸውም ተነግሯል።

ሌሎች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በአዲስአበባ፣ ቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ ባህርዳር እና ሐዋሳ ሳይቶች በማስገንባት ላይ መሆኑም በመርሃ ግብሩ ተገልጿል።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በአገሪቷ ካሉ የግንባታ ኩባኒያዎች መካከል አንዱ ሲሆን ባለፉት ጊዜያት የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ እና የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የግንባታ ስራዎችን ማከናወኑ እና በማከናወን ላይ መሆኑም ተገልጿል።

የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 459/2012 እንደገና የተቋቋመ እና የሰራዊት አባላትን ኑሮ ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራትን የሚያከናውን እንዲሁም የሰራዊቱን ሞራል ለመጠበቅና ለማጎልበት የሚያግዙ ልዩ ልዩ ተግባራትን የሚያከናውን መንግስታዊ የልማት ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም