የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የሚያቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

91

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ቀውስ ለገጠማቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኅብረት የሰብዓዊ መብት ልዩ መልዕክተኛ ኤመን ጊልሞር ገለጹ።

የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ መብት ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለመመልከት በኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝታቸውም ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የረድኤት ድርጅቶችን እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

ጉብኝታቸውም በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ከእነዚህ አካላት ጋር ፍሬያማ ውይይትና ማድረጋቸውን ነው ልዩ መልዕክተኛው የጠቆሙት።

በዚህም በተለይም ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል የተደረሰው የተኩስ ማቆም ውሳኔ ኅብረቱ በአዎንታ እንደሚቀበለው ገልጸው፤ ሰብዓዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመው የሰብዓዊ ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት ኃሳባቸውን አጋርተዋል።

ከዚህም አንጻር የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ቀውስ ለገጠማቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው ለዚህም ሙሉ ፍቃደኛ ነው ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት በፈጸሙ አካላት ላይ መንግሥት ተጠያቂነት የማስፈኑ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄደው የሠላም ሂደት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ