“የአማራ ክልልን ለማዳከም የሚሰሩ የውስጥ ጠላቶች እንዳሉ በጥናት ደርሰንበታል” -ዶክተር ይልቃል ከፋለ

141

ባህርዳር፤ ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የአማራ ክልልን ለማዳከምና ለመከፋፈል የሚሰሩ የውስጥ ጠላቶች እንዳሉ ባደረግነው ጥናት ደርሰንበታል” ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

“የአማራ ክልል መንግስት ስርዓት አልበኞችን ስርዓት የማስያዝ፣ ሕግን የማስከበርና ሕገ ወጦችን የመቆጣጠር ሙሉ አቅም አለውም” ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ “በወቅታዊ የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ” ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በአማራም ሆነ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጸጥታ ስጋት የደቀነው ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው” ብለዋል።

የአማራ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባደረገው ጥናትና ግምገማ “የክልሉን ህዝብ ውስጣዊ አንድነት የሚረብሽ፣የሚያዳክም፣የሚከፋፍልና እርስ በእርስ እንዲጋደል የሚሰሩ የጠላት ቡድኖች” እንዳሉ ደርሶበታል ሲሉ ገልጸዋል።

ቡድኖቹ በሚፈጽሙት ድርጊት ዜጎች በገጠርና በከተማ ህዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮውን በአግባቡ እንዳይመራና የልማት ስራዎች ላይ እክል የሚፈጥሩ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን አመልክተዋል።

የኢንቨስትመንትና ሌሎች መንግስታዊ ስራዎች እንዳይከናወኑ እንቅፋት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች እየታዩ መጥተዋል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው።

የሕገ ወጥ ንግድ መበራከት፣ምርቶችን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር፣ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የጥይት ተኩስና መሰል ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች በክልሉ እየተስተዋሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

በየቦታው የታጠቀም ሆነ ያልታጠቀ ኃይል በጉልበት የመዝረፍና ሰው ማገት እንዲሁም ሕዝብን እርስ በእርስ በሃይማኖት፣ በብሔርና መሰል ጉዳዮች በመከፋፈል ወደ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

እየተፈጸሙ ያሉት ሕገ ወጥ ተግባራት ሕዝቡን የጸጥታ ስጋት ውስጥ በመክተቱ የክልሉ መንግስት “ጠንካራ የሆነ” የሕግ ማስክበር ስራ መጀመሩንና ሕገ ወጦችን በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ሕግ ማስከበሩ የአማራ ክልልን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ የሕብረተሰቡን የጸጥታ ስጋትና ተንቀሳቅሶ የመስራት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ተናግረዋል።

“የክልሉ መንግስት ሕገ ወጦችን የመቆጣጠር፣ስርዓት አልበኞችን ስርዓት ለማስያዝና ሕግ የማስከበር ሙሉ አቅም አለው” ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

“እኔም ለብቻዬ ወታደር ይኖረኛል የሚል ኃይል” የክልሉ መንግስት አይታገስም ያሉት ዶክተር ይልቃል “በክልሉ ከፋኖ ጋርና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚናፈሰው ወሬ ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች አጀንዳ በመሆኑን ሕብረተሰቡ ከመሰል ማደናገሪያ መጠበቅ አለበት” ነው ያሉት።

ሕብረተሰቡ የጦር መሳሪያን እንዲመዘገብ የተሰጠው እድል መሳሪያን በተደራጀ አግባብ ለመምራት እንዲቻልና ተገቢውን ስልጠና በመስጠት ዝግጁ እንዲሆን ለማድረግ እንደሆነም አክለዋል።