ኢትዮ ቴሌኮምና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በ"ደራሽ" የክፍያ ስርዓት አማካኝነት የውሃ አገልግሎት ክፍያን በቴሌ ብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

248

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮ ቴሌኮምና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በ"ደራሽ" የተቀናጀ የክፍያ ስርዓት አማካኝነት የውሃ አገልግሎት ክፍያን በቴሌ-ብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

"ደራሽ" የተቀናጀ የክፍያ መረጃ ስርዓት በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የበለጸገ መተግበሪያ ሲሆን፤ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች በሚመቻቸው መንገድ እና በመረጡት ቦታ የአገልግሎት ክፍያ፤ግብር፤ኪራይ እና ቅጣት መክፈል ያስችላቸዋል፡፡

የዛሬው ስምምነትም መተግበሪያውን ከቴሌ ብር ጋር በማስተሳሰር የውሃ ክፍያ አገልግሎት በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል ነው፡፡

አገልግሎቱ ተግባራዊ የሚሆነው በባህርዳር ፣ደሴ፣ አርባ ምንጭ ፣ ኮምቦልቻ፣ እንጅባራ፣ ፍኖተ ሰላም ከተሞችና ሀረሪ ክልል መሆኑ ተጠቅሷል።

በዚህም የውሃ አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች ''ደራሽ'' በተሰኘ መተግበሪያ አማካኝነት የደንበኞቻቸውን ወርሃዊ ሂሳብ በቴሌ-ብር ለመሰብሰብ የሚያስችላቸው ይሆናል።

ይህም የማህበረሰቡን የዲጂታል ክፍያ ተጠቃሚነት ፍላጎት ለማሳደግ ፣በጥሬ ገንዘብ የሚደረገውን ግብይት ለመቀነስና የቢዝነስ መረጃዎችን ፍሰት በቀላሉ ለማወቅና ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተነስቷል።

የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህወት ታምሩ በዚሁ ወቅት ኩባንያው ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ተግባራዊ ሲደረግ በሰባቱ ከተሞች የሚኖሩ የቴሌ-ብርና የደራሽ ደንበኞች በቀላሉ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በመቆጠብ ሂሳባቸውን መክፈል እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚተገበር ሳይሆን ሂደት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ዛሬ የተደረገው ስምምነት የጥረቱ አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው፣ተቋሙ በዋናነት የኢትዮጵያን  የዲጂታልና የሳይበር ሉዓላዊነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በዚህም አቅም ባልተፈጠረባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ በመሳተፍ ዜጎችን ለመድረስ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ቴክኖሎጂን የማበልጸግ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በመሆኑም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት እንደሆነ በማንሳት፣ ተቋሙ በዚህ ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በተቋሙ በኩል የለማው 'ደራሽ' የክፍያ መተግበሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውንም የክፍያ ስርዓት ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም የቴሌ-ብር አገልግሎትን ተግባራዊ ማድረጉ ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን አዲስ የአኗኗር ዘይቤ በመፍጠርና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን ማስፋፋት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ኩባንያው ከዚህ ቀደም ከበርካታ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌ-ብር ለመፈጸም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን በአገልግሎቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ19 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማፍራት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም