የረቀቀ የሙስናና ሌብነት ወንጀልን ለመከላከል ሁኔታውን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል

209

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የረቀቀ የሙስናና ሌብነት ወንጀልን ለመከላከል ሁኔታውን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።

ፍትህ ሚኒስቴር ከስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር “የባለድርሻ አካላት የሙስና መከላከል ቅንጅት በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቴዎስ እና የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የክልል የስራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

በቅርቡ በተካሄደ አገራዊ ጥናት ከሰላም እጦትና ከኑሮ ውድነት ቀጥሎ ሙስና በ3ኛ ደረጃ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄ መሆኑ ተመላክቷል ነው የተባለው ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደሚሉት፤ ሙስና በአሁኑ ወቅት ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚካሄድበትና ቀላል የማይባሉ ተንቀሳቃሽና ቋሚ ንብረቶች የሚዘረፉበት ወንጀል ሆኗል።

የረቀቀውን የሙስናና የሌብነት አካሄድን ለመከላከል ወቅቱን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው፤ የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቲዮስ በሰጡት ማብራሪያ የማህበረሰቡ አንገብጋቢ ችግር የሆነውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሙስናን መዋጋት የዘመቻ ስራ ሳይሆን በቀጣይነት የሚከናወን ተግባር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው የአገሪቱን እድገት ወደ ኋላ ከጎተቱ አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው የሙስና ወንጀል እየተስፋፋ መምጣቱን አመልክተዋል።

በተለይ አገርን በማውደም ደረጃ የሚመደቡ የሙስና ተግባሮች እየተስፋፉ እንደሆነ አመልክተዋል።

የተደራጁ ሙሰኞች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እየበዘበዙ በመምጣታቸው ጉዳዩን አሳንሶ ማየት ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ችግሩን ለመፍታት በባለቤትነት ሊይዘውና ሊከታተለው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።