በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤና ጣቢያ ደረጃ የካንሰር ቀዶ-ህክምና አገልግሎት መስጠት ተጀመረ

122

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የጡትና የማህጸን በር ካንሰር ቀዶ-ህክምና አገልግሎት በጤና ጣቢያ ደረጃ መስጠት መጀመሩን የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገለጸ፡፡

ቸርችል ጤና ጣቢያ ቀዳሚው የጡትና የማህጸን በር ካንሰር ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት የጀመረ ጤና ጣቢያ ሆኗል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም ደነቀ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የጡት ካንሰር እና የማህጸን በር ካንሰር ቀዶ ህክምና በጤና ጣቢያ ደረጃ መጀመሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የካንሰር በሽታ ህክምና ላይ ያለውን ችግር ለመቀነስ ያግዛል፡፡

በዚህም በጤና ጣቢያው የጡት እና የማህጸን በር ካንሰር ቀዶ ህክምና በአጠቃላይ ከልየታ ጀምሮ ምርመራ፣ ቀዶ ህክምናና ክትትል ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የጡት ካንሰር እና የማህጸን በር ካንሰር ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስፋፋት እንዳለበት ጠቅሰው በተቀናጀ መንገድ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር እንዳለ አንበርብር በበኩላቸው፤ በቸርችል ጤና ጣቢያ ለሁለት የጡት እና የማህጸን በር ካንሰር ታማሚዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ካንሰርን ለማከም፤ ካንሰሩ ያለበትን ደረጃ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ህመሙ የመጀመሪያው የካንሰር ደረጃ ላይ ከሆነ በቀላሉ የስርጭት መጠኑ ሳይጨምር በቀዶ ህክምና ማከም እንደሚቻል ዶክተር እንዳለ ተናግረዋል፡፡

የቸርችል ጤና ጣቢያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገላና ሉሉ በበኩላቸው፤ የብዙ እናቶችን ህይወት እየቀጠፈ  ስላለው የካንሰር በሽታ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጤና ጣቢያው ከካንሰር ህሙማን ልየታ ጀምሮ የቀዶ ህክምና መሰጠት መጀመሩ ችግሩን ለማቃለል ከፍ ያለ እገዛ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት የጡት ካንሰር ህክምና ተጠቃሚ የሆነችው ቤዛዊት ገሰሰ፤ በጤና ጣቢያው ለተደረገላት ህክምና ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡

የቀዶ ህክምና አገልግሎቱ  በጤና ጣቢያ እንዲጀመር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አጋር ድርጅቶች እና  ተቋማት በወቅቱ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም