ባለሀብቶች የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

146

ጋምቤላ፤ ግንቦት 10/2014(ኢዜአ)፡ በጋምቤላ ከተማ በኢንዱስትሪ ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ።

በባለሀብቶች የሚነሱ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጀሉ አስታውቀዋል።

የክልሉን ኢንዱስትሪ ምርታማነት ለማሳደግ ‘‘ኢትዮጵያ ታምርት’’ በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ የስራ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች የተሳተፉበት ምክክርና የመስክ ንቅናቄ መረሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተገኙት ባለሀብቶች መካከል የጉር ዱቄት ፋብሪካ ባለቤት አቶ ሰለሞን ደበበ የውሃና የኤሌክትሪክ መብራት መሰረተ ልማት ችግር በስራቸው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

የጋምቤላ ከተማ የሚያ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ስራአስኪያጅ አቶ አድማሱ ዋክኒ በበኩላቸው  የመብራት መቆራረጥና የውሃ ችግር በእለት ከእለት ስራቸው ላይ ጫና መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ባለሀብቶቹ መንግሥት  በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ሊፈታላቻው እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ መጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በባለሀብቶች የሚነሱ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዘረፉ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ የኢንዱስተሪ ንቅናቄ መረሃ ግብሩ መካሄዱን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊው አቶ ኦኬሎ ኡቦንግ ገልጸዋል።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቲቾት ኮመዳን በበኩላቸው ቢሮው 100 ሄክታር መሬት ተረክቦ የማልማት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ቢሮው በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።  

በጋምቤላ ክልል 78 ያህል የተለያዩ አነስተኛና መካከለኛ እንዲስትሪዎች እንደሚገኙ በመረሃ ግብሩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም