በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የክልሉን የፍራፍሬ ምርት ወደ ቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ ይሰራል- ወይዘሮ ሚስራ አብደላ

181

ሐረር፤ ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የክልሉን የፍራፍሬ ምርት ወደቀድሞ ሁኔታ መመለስ በሚያስችል መልኩ እንደሚከናወን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ሚስራ አብደላ ገለጹ።

በክልሉ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ እና ሌሎች ችግኞች እንደሚተከሉም ጠቁመዋል።

በመጪው ክረምት የአካባቢውን ማህበረሰብ አርሶ አደር ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እና በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተመናመኑ የሚገኙ የፍራፍሬ ዝርያዎችን ወደ ቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ገልጸዋል።

May be an image of plant and outdoors

የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚረዱ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው በዚህም መቶ ሺህ የተሻሻሉ የአቦካዶ ዝርያዎችን የማዳቀል ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

ክልሉ የሚታወቅበት የሐረር ቡናን ወደ ቀድሞ ልማቱ ለማምጣት የቡናችግኝ የማፍላቱ ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዚህም ችግኞቹ ጸድቀው ውጤታማ እንዲሁም በባለቤትነት የመንከባከብ ስራ እንዲከናወን ከማድረግ አንጻር የክትትል ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በሐረሪ ክልል ባለፉት ሶስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉት 7 ሚሊየን ችግኞች ውስጥ 73 በመቶው መጽደቃቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም