መንግስት ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር መክፈሉን ገለጸ

140

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት በዘንድሮ በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር መክፈሉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከመደበኛ በጀት 26 ቢሊዮን ብር የሚያስወጡ አዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች ወደ 2015 ዓ.ም በጀት አመት እንዲዛወሩ መደረጋቸውንም አመልክቷል።

የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የ2014 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ ተካሄዷል።

በዘጠኝ ወሩ ለውጭ ብድር 24 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ታቅዶ 20 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መከፈሉን አስታውቋል።

10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ብድርን ለመክፈል ታቅዶ 17 ቢሊዮን ብር እንደተከፈለም አመልክቷል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከውጭ 2 ቢሊዮን ዶላር ብድርና እርዳታ ለማግኘት ታስቦ ከ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር መገኘቱ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል የፌዴራል መንግስት የበጀት ጉድለትን ለማጥበብ እንዲሁም የአገር ውስጥ ብድር እንዳይጨምር ለማድረግ በተወሰደው እርምጃም ከመደበኛ በጀት 26 ቢሊዮን ብር የሚያስወጡ አዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች ወደ ሚቀጥለው በጀት አመት እንዲዛወሩ መደረጋቸውን የዘጠኝ ወር ሪፖርቱ አሳይቷል።

በተጨማሪም የአምስት ቢሊዮን ብር የወጪ ቅነሳ መደረጉ ተገልጿል።

መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የምግብ ሸቀጦች ያለ ውጪ ምንዛሬ ፈቃድ (ፍራንኮቫሉታ) እንዲገቡ በመደረጋቸውና በምግብ ሸቀጦች ላይ ጥሎት የነበረውን ታክስና ቀረጥ በማንሳቱ በዘጠኝ ወሩ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሳይሰበሰብ መቅረቱን አመልክቷል።

የስንዴ ዋጋን ለማረጋገት 320 ሺህ ቶን ስንዴ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉንና የምግብ ዘይትን በተመለከተም ገበያውን ለማረጋጋት የምግብ ዘይት ግዢ ውል መፈጸሙን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ፣ የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን እንዲሁም የመንግስት ግዢ አገልግሎት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸማቸው ግምገማና ውይይት ተደርጎበታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም