የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግሮችን መከላከል፣ ሰብአዊ ድጋፍና የአብሮነት ጉዳዮችን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው ሊሰሩ ይገባል

125

ግንቦት 10/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግሮችን መከላከል፣ ሰብአዊ ድጋፍን ተደራሽ ማድረግና አብሮነትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

የሚዲያ ተቋማት የመልዕክት ቀረጻቸውን ከነዚሁ ጉዳዮች ጋር አስተሳስረው ሊሰሩ እንደሚገባም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር "ሰብዓዊነትና የሚዲያ ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ከሚዲያ ተቋማትና ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በሀገሪቱ ተፈጥረው በነበሩ ልዮ ልዮ ችግሮች ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፎች ተደራሽ እንዲሆኑ የሚዲያው ሚና ከፍተኛ ነበር።

ችግሮችን በመከላከል፣ ግንዛቤ በመፍጠርና አውነታዎችን በማመላከት ረገድ ሚዲያ ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የሀገሪቱ ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግሮችን መከላከል፣ ሰብአዊ ድጋፍና የአብሮነት ጉዳዮችን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝትና ኮሚኒኬሽን መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በበኩላቸው ሚዲያው ሰብአዊ ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት ጋር በመቀራረብ መልዕክት ቢቀርጽ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።

የመልዕክት ቀረጻውን የአንድ ጊዜ ዘመቻ ከማድረግ ባለፈ ዕቅድ በመንደፍ ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

መንግስት ከሚያደርገው የሰብአዊ ድጋፍ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ያሉ ድጋፍ ሲጪዎችም በተግባሩ እንዲሳተፉ ማነሳሳት አስፈላጊ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር መኩርያ አሳስበዋል፡፡

ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ የሚጠይቁ ጉዳዮች ባሉበት በዚህ ወቅት ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ሚዲያዎች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ያሉት ደግሞ የዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጉሴ መሸሻ ናቸው።

በተጨማሪም በሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ የሚመለከታቸውን አካላት ማስተባበር እንዲሁም በዘርፉ የፖሊሲ ክፍተቶች ካሉ መጠቆም የሚዲያው ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ረገድ የሚዲያ ሃላፊዎች ባለሙያዎችን የማስተባበርና የመምራት ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም