ባለፉት አሥር ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ 418 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል

69

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት አሥር ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ከ 418 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር የ2014 በጀት ዓመት የአሥር ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበልን ጨምሮ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበላይ አመራሮችና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት አሥር ወራት የማምረት አቅምን ለማሳደግ የሰራቸው ሥራዎች አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ባለፉት አሥር ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የኢንዱስትሪ ምርቶች 498 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 418 ሚሊየን ዶላር መገኘቱ ተጠቁሟል።

አፈጻጸሙ የእቅዱን 84 በመቶ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር  የ32 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተገልጿል።

ከእቅድ አንጻር ምግብ መጠጥና ፋርማሲዩትካልስ 102 በመቶ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 85 በመቶ እንዲሁም ቆዳና የቆዳ ውጤቶች 38 በመቶ ማሳካት መቻላቸው ተመላክቷል።

እንዲሁም የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት 188 በመቶ፣ ስጋና ወተት 119 በመቶ በማሳካት ከፍተኛ አፈጻጸም ሲያስመዘግቡ፣ ኤሌክትሮኒክስና ኢንጂነሪንግ 37 ነጥብ 4 በመቶ ማሳካታቸው ተገልጿል።

በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት 5 ሺህ 094 ኢንዱስትሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 4 ሺህ 630 ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውም ተመላክቷል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጀመረው “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄም ሥራ አቁመዉ ከነበሩ 446 አምራቾች ውስጥ 118  ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲመለሱ መደረጉም ተገልጿል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉን በስፋት ማነቃቃት መቻሉን ገልጸዋል።

በሁሉም ክልሎች በተካሄዱ መድረኮች ባለኃብቶችን ማቀራረብና አሉ የተባሉ ተግዳሮቶችን በጋራ መለየት መቻሉን ገልጸዋል።

በአሥር ወራት ውስጥ የተገኘው 418 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ102 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል።

በምግብና መጠጥ በኩልም በአሥር ወራት ውስጥ የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበበት ዘርፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቀጣዮቹ ሁለት ወራት በሁሉም ከእቅድ አንጻር ጠንካራ አፈጻጸም ለማምጣት ርብርብ እንደሚደረግም አክለዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ በሉልታ በበኩላቸው፤ ባለፉት አሥር ወራት ለ180 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታስቦ 158 ሺህ ለሚሆኑት የሥራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

ይህም በአዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍና የነባሩን ኢንዱስትሪ በማጠናከር የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።

በአገሪቷ ካለው የሥራ-አጥ ቁጥር አንጻር በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ በአሥር ዓመት ውስጥ ለ 5  ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም አመላክተዋል።