ፍርድ ቤቱ በኢድ አል-ፈጥር በዓል ላይ የአድማ ብተና የጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል በተጠረጠረው የፖሊስ አባል ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

286

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኢድ አል-ፈጥር በዓል ላይ የአድማ ብተና የጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል በተጠረጠረው የፖሊስ አባል ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

በተጠርጣሪው ላይ መረጃ የማሰባሰቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪው ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቧል።

የፌደራል ፖሊስ አድማ ብተና ዘርፍ አባል የሆነው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ በኢድ አል-ፈጥር በዓል ከፈነዳው የአድማ በታኝ የጭስ ቦንብ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑ  የሚታወቅ ነው።

በመሆኑም ጉዳዩን የያዙት መርማሪ ፖሊሶች ከዚህ በፊት በተሰጣቸው የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ ያካሔዱትን ተግባራት ለችሎቱ አቅርበዋል።

የምስክሮችን ቃል የመቀበል፣ ተጠርጣሪው የሚጠቀምባቸውን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እንዲመረመሩ ለብሔራዊ መረጃ ደሕንነትና ለኢትዮ-ቴሌኮም ደብዳቤ መላክን ጨምሮ የኃላፊዎችን ቃል የመውሰድ ስራቸውን አከናውነናል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ተጠርጣሪው ከጀርባው የገንዘብ ድጋፍ እንዳለው ለማጣራትም ለባንኮች ደብዳቤ መፃፉንም  ነው ያስታወቁት።

በቀጣይም ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማጠናቀቅ፣ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋልም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልግም ነው ያመለከቱት።

ተጠርጣሪው በበኩሉ ''የፈነዳው የጭስ ቦንብ በአጋጣሚ እንጂ ሆን ብዬ የፈፀሙኩት ጉዳይ አይደለም፣ በእለቱ ከሌሊት ጀምሮ ሕዝብን በማገልገል ስራ ላይ ነበርኩ፤ ምንም አይነት ወንጀል አልሰራሁም'' ሲል ተከራክሯል።

በመሆኑም የዋስትና መብቴ  ተከብሮ ጉዳዩን በውጭ ሆኜ እንድከታተል ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በእለቱ ከተመደበበት የስራ ምድብ አካባቢ ውጭ የነበረ ሲሆን የአስለቃሽ ጭስ ቦንብ ይዞ ሕዝብ መሃል መቆም እንደማይቻልም ነው መርማሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ  ያስረዱት።

በእለቱ የፈነዳው የአስለቃሽ ጭስ ብዛት ሶስት እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ የገለጹት መርማሪዎቹ ተጠርጣሪው እንደሚለው አንድ ብቻ አለመሆኑንም ለችሎቱ አብራርተዋል።

በመሆኑም አስለቃሽ ጭሱ በመፈንዳቱ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ መነሻነት ከፍተኛ ንብረት መውደሙን ገልጸዋል።

የግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ቀሪ የምርመራ ስራውን ለማጠናቀቅ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ 13ቱን በመፍቀድ ለግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም