ሴቶች ግጭቶችን በማርገብና ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ያላቸውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

190

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2014 /ኢዜአ/ ሴቶች ግጭቶችን በማርገብና ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ያላቸውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አመራር አባላት ጥሪ አቀረቡ፡፡

የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ለኢዜአ እንደገለጹት ሴቶች በተፈጥሮና በሕይወት ልምዳቸው ግጭቶችን በመከላከል ሰላምን ለማስፈን እንደ አገር የማይተካ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ሰላም የሚያደፈርሱ ጉዳዮችን በመከላከል እንደ አገር የነበራቸውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ከልቱምባ በክር ሴቶች ሰላምን የሚያውኩ አካላትን በመቃወም በኩል ብርቱ ትግል ሲያደርጉ እንደነበር አንስተዋል።

ሊጉ ከሰላም ጋር የተያያዙ ስራዎችን በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጠልም አረጋገጠዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አማራ ክልል ቅርንጫፍ ሴቶች ሊግ ኃላፊ ኢሌኒ አባይ በበኩለቸው ሴቶች በብሔርና ሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በመታገል ረገድ የጀመሩትን ጥረት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም ሴቶች ግጭቶች እንዳይከሰቱ በመከላከል ረገድ አበረታች ተግባር እያከናወኑ ስለመሆኑም ነው ያብራሩት፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ሴቶች ሊግ ኃላፊ መብራት ባጫ፤ ኢትዮጵያ ልማቷን እንዳታከናውን በሚሹ አካላትን ግጭቶች እንዳይነሱ ሴቶች ስለሰላም አብዝተው መስራት እንዳለባቸው አውስተዋል።

ሴቶች በግጭት ወቅት ይበልጥ ተጎጂዎች እንደሆኑ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ግጭት የሚቀሰቅሱ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆኑና የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም ሴቶች ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የነበራቸውን ሚና አጠናክረው ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አባላቱ ተናግረዋል።

ሰላምን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም