በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ የሀሰት መረጃዎች ውስብስብ እየሆኑ በመምጣታቸው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል--ምሁራን

96

አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 09/2014 (ኢዜአ)በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች እየተወሳሰቡ በመምጣታቸው ህብረተሰቡ መረጃዎችን አጣርቶ በመቀበል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ምሁራን አስገነዘቡ ፡፡

ሰሞኑን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው 8ኛ ሀገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት ላይ የተሳተፉ ምሁራን በማህበራዊ ትስስር ገጾች አጠቃቀምን ላይ ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ በተመለከተ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ትምህርት መምህርት ሙና ሱሌማን እንዳሉት በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚለቀቁ የሀሰት መረጃዎች እየተበራከቱና እየተወሳሰቡ በመምጣታቸው ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡

 ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች እየተበራከቱና እየተወሳሰቡ በመምጣቱታቸው በርካታ ሰዎች የጉዳቱ ሰለባ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

"በተለይ ወጣቶችን ከምክንያታዊነት እያስወጣ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመምራት ወደተዛባ መንገድ እንዲያተኩሩ እያደረገ ይገኛል" ብለዋል፡፡

"በተለይ ወጣቱ ላይ ብዙ መሰራት ያስፈልጋል" ያሉት መምህርቷ፤ወጣቱ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚያገኛቸውን መረጃዎች  መርምሮና በደንብ አጣርቶ መቀበል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

"ወጣቱ በስሜታዊነት ተነሳስቶ ወደአልሆነ ድርጊት እንዳይገባ  የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራት ተጠናክረው መሰራት አለባቸው" ሲሉ አመልክተዋል ።

በምህርቷ አክለው "ባልተገቡ መረጃዎች ምክንያት ከሚደርስ አደጋ ለመጠበቅ የምንጩን ተአማኒነትና የመረጃውን ትክክልኛነት ማረጋገጥ፣ የመረጃውን መልእክት ምን እንደሆነ በሰከነ መንገድ መገምገም  ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል፡፡

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ኮሌጅ መምህር የሆኑት ገላን ገብሬ በበኩላቸው ትክክለኛ መረጃ በማህበረሰቡ ዘንድ እምነት እንደሚፈጥር ሁሉ የተዛባ መረጃን እንዳለ መቀበልም በግለሰብም ሆነ በሀገር ላይ ጉዳት እንዳለው ገልጸዋል ፡፡

በአሁኑ ወቅት በማህራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ መረጃዎች በይዘትም ሆነ በስልት እየተወሳሰቡ መምጣታቸውን የተናገሩት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና መምህር ዘርሁን አያሌው ናቸው፡፡

"የተለያዩ የፖለቲካ  ትርፍ አገኛለሁ በሚል ዕሳቤ ብቻ በገጾች ላይ የተዛባ መረጃን በመልቀቅ ሰላምን ለማደፍረስ ከሚጥሩ ግለሰቦች መጠንቀቅ ይገባል" ብለዋል።

የተለቀቁ መረጃዎችን ማን እንደለቀቃቸውና ለምን አላማ እንደተለቀቁ  መመርመር እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ወቅቱ የሚጠይቀውን ንቃት መያዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም