በየካ ክፍለ ከተማ ከ300 በላይ አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቤት እድሳት መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ

103

ግንቦት 9/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ በየካ ክፍለ-ከተማ የሚኖሩ ከ300 በላይ አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጎ ፈቃድ ቤት እድሳት መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ በክፍለ ከተማው በመገኘት  የቤት እድሳት እንዲሁም ሌሎች የልማት ስራዎችን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ዋና ስራ አስኪያጁ በዚህን ወቅት ከተማ አስተዳደሩ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የመዲናዋን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በመለየት ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ክረምት ከመግባቱ በፊት የሚከናወኑ ስራዎች መለየታቸውን ጠቅሰው፤ የቤት እድሳት እና የምገባ ማዕከላት  ግንባታ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ስራዎች ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡

በክፍለ ከተማው ሶስት የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካዎች ለመገንባትም ከባለሀብቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መራጊያው ተበጀ  በበኩላቸው ክፍለ ከተማው የነዋሪዎችን ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሚቀጥሉት ሶስት ወራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ1 ሺህ 500 በላይ  ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ የሚመገቡባቸው ሁለት የምገባ ማዕከላት እንደሚገነቡም ተናግረዋል፡፡፡

በዛሬው እለት ደግሞ በክፍለ ከተማው የሚኖሩ ከ300 በላይ አቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤቶች የማደስ ስራ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በክፍለ ከተማው የተጀመሩ የልማት ስራዎች እውን እንዲሆን የነዋሪዎችና ባለሀብቶች ተሳትፎ የላቀ ሚና እንዳለውም አብራርተዋል፡፡

ወይዘሮ ታደለች ይመር የቤት እድሳት ከሚደረግላቸው ነዋሪዎች መካከል አንዷ ሲሆኑ፤ በአካባቢው በተከሰተ የእሳት አደጋ የመኖሪያ ቤታቸው መጎዳቱን ይናገራሉ፡፡

በዚህም አስቸጋሪ ህይወት ሲገፉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የእድሳት መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመመረጣቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡