የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ለ13 ተቋማት እውቅና ሰጠ

143

ግንቦት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዓለም አቀፍና ብሔራዊ የአክሬዲቴሽን መስፈርት ላሟሉ ስድስት የህክምና፣ ሶስት የፍተሻ ላቦራቶሪ፣ ሶስት የኢንስፔክሽን እና ለአንድ የሰርተፊኬሽን በጥቅሉ ለ13 ተቋማት እውቅና ሰጠ፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ፍስሐ የአክሬዲቴሽን አጽዳቂ ኮሜቴ የተቋማቱን ሰነድ በመፈተሽና በመስክ ምልከታ በመገምገም እውቅና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቋማት የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ለማግኘት የሚያደርጉት ተነሳሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህም የአገሪቱን ምርትና አገልግሎት ተዓማኒነትና ተቀባይነት ለመጨመር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የእውቅና ሰርተፍኬቱ ለአንድ ዓመት እንደሚያገለግል የገለጹት አቶ አርዓያ፤ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለ130 ተቋማት የአክሬዲቴሽን አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል።

ዛሬ ምስክርነት የተሰጣቸው ነባርና አዳዲስ 13 ተቋማትም የጥራት ደረጃቸውንና ያገኙትን እውቅና ጠብቀው እንዲያስቀጥሉና ለተገልጋያቸው መልካም አገልግሎት ለመስጠት ተግተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ላይ "የእውቅና ሰርተፍኬት ያለው" እየተባለ የሚተዋወቅን ማስታወቂያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ተገቢውን ቁጥጥር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ካገኙ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ተሻለ በልሁ፤ አክሬዲቴሽኑ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳ ምርትና በአግሮ ፕሮሰሲንግ የላቦራቶሪ ምርት ላይ በሚሰራቸው የተስማሚነትና ምዘና ስራዎች ላይ ትክክለኛነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዓማኒ እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል።

ካሁን በፊት የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ባላገኙ ድርጅቶች የሚላኩ ምርቶች ውድቅ ሲደረጉ እንደነበር አስታውሰው፤ አክሬዲቴሽኑ መሰጠቱ ለሀገር ጥቅምና ገጽታ ግንባታ ፋይዳው የላቀ እንደሆነ አንስተዋል።

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የላቦራቶሪ ክፍል ኃላፊ አቶ ተመስገን ሲሳይ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ "በሄማቶሎጂ" እና "ክሊኒካል ኬሚስትሪ" የፍተሻ ወሰኖችን አሟልቶ የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ተቋሙ ተገልጋዮች የሚያነሱትን ቅሬታ ለመቅረፍ እንደሚያስችለው ገልጸው፤ ሆስፒታሉ በሌሎች ዘርፎች የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ለማግኘትና ቅሬታ የማይነሳበት አገልግሎት ለህዝቡ ለመስጠት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም