በክልሉ ከ341 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ – ቢሮው

157

ሚዛን አማን ግንቦት 09/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዘንድሮ ከ341 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚከተሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ኮንታ ዞን ከ58 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተከላ የሚከናወንበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ጨካ ቦቻ ቀበሌ መርሐ ግብሩን ችግኝ በመትከል አስጀምረዋል።

አቶ ማስረሻ በችግኝ ተከላው ወቅት እንዳሉት ክልሉ ከፍተኛ የብዝኃ ሀብቶች ባለቤት ቢሆንም፤ በጎደለው እየሞሉ የተፈጥሮ ሀብቱን መጠበቅ ያስፈልጋል።

የክልሉ ነዋሪዎች የተፈጥሮ ሀብትን የመንከባከብና የመጠበቅ የቆየ ልምዳቸውን በመጠቀም ደንን ዘላቂና አስተማማኝ ሀብት አድርገው እንዲቆዩ አስገንዝበዋል።

አካባቢው “ደን ህይወት ነው” ብለው አባቶችና ቅድመ አያቶች ያቆዩትን በጎ ባህልና ታሪክ ተረክበው በእምነት የሚሰሩ ህዝቦች ያሉበት መሆኑን ገልጸዋል።

 በክልሉ  በተያዘው ዓመት 341 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውና የጥምር ደን እርሻ ችግኞችን በማዘጋጀት በበልግና በክረምት ወቅቶች ለመትከል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

“እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ችግኞች በመንግሥት፣ በግብረ ሰናይ ድርጅቶችና በአርሶ አደሮች ተዘጋጅተዋል” ብለዋል።

በክልሉ ሁሉም ዞኖች የችግኝና የጉድጓድ ዝግጅት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ማስረሻ አስታውቀዋል።

በዋናነት አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ግራቪላና ሌሎች መሰል ተጨማሪ የምርት ፋይዳ ላላቸው ችግኞች ላይ ትኩረት  መሰጠቱን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር የተያዘው ችግኝ የመትከል ዘመቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክብረ ወሰንን ከማስመዝገብ ባለፈ፥ የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅና የግብርና ምርት ማሳደግን አላማ አድርጎ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ በችግኝ ተከላ ዘመቻ እያሳየ ያለውን መነሳሳት የተተከለው ችግኝ እንዲፀድቅና ውጤት እንዲያስገኝ ክትትልና እንክብካቤ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በዞኑ ከ4 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

የሙዝ፣ የፓፓያ፣ የአናናስ፣ የማንጎ አቡካዶ ችግኞችን ጨምሮ ሌሎች ሥነ ምህዳር እየጠበቁ ምርት የሚሰጡ የዛፍ ዝርያዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው አመልክተዋል።

ለተከላ የሚሆኑ ጉድጓዶች በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።

መርሐ ግብሩን ለማሳካት የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም ሃላፊው አስታውቀዋል።