ዘላቂ ሰላምን በማስፈን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የመንግስታት ግንኙነት መጠናከር ወሳኝ ሚና አለው

70

ግንቦት 9/2014/ኢዜአ / በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የመንግስታት ግንኙነት መጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተጠቆመ፡፡

አገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች የግንኙነት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል፡፡

የመንግስታት ግንኙነት ሥርዓት የፌደራልና የክልል መንግስታት በመካከላቸው፣ እንዲሁም የክልል መንግስታት በጋራ ወይም በጣምራ በተሰጣቸው ስልጣንና በሚያከናውኗቸው ጉዳዮች ላይ የሚመሰረቱት የተዋረድ ወይም የጎንዮሽ ግንኙነት ነው፡፡

በኢትዮጵያም ይህ ግንኙነት በተደራጀ መልኩ የሚመራ የህግ ማእቀፍ ያልነበረ ሲሆን፤ በ2013 ዓ.ም ግንኙነቱን የሚመራ አዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

አዋጁ ስድስት አደረጃጀቶች ሲኖሩት፤ ከእነዚህም ውስጥ  አገር-አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች ግንኙነት መድረክ በዛሬው እለት ተገናኝቶ ውይይቱን አካሂዷል፡፡

አገር አቀፍ የህግ አውጪዎች ግንኙነት መድረክ፤ አገር-አቀፍ የህግ አስፈጻሚዎች ግንኙነት መድረክ፤ አገር-አቀፍ የአስፈጻሚዎች ዘርፋዊ ግንኙነት መድረክ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤትና የክልሎች ግንኙነት መድረክ  እንዲሁም የክልል መንግስታት የግንኙነት መድረኮች ደግሞ ቀሪ አደረጃጀቶች ናቸው፡፡  

የመንግስታት ግንኙነቶች የጋራ ኃላፊነቶችን በአግባቡ ለመወጣት፣ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት እንዲሁም በጋራ ልማትን ለማረጋገጥ ዓላማ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡

በዛሬው የውይይት መድረክም በተለይ ፍርድ ቤቶች በጋራ የሚመሰርቱት የህግ ተርጓሚዎች የግንኙነት መድረክ ፍትህን ለማስፈን፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ግጭቶች እንዳይከሰቱ ከማድረግ አንጻር ሰፊ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡

ውይይቱን አስመልክተው ሃሳባቸውን የሰጡት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሀራ ሁመድ እንዳሉት፤ አገር-አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ግንኙነት ተቀራራቢ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ያለው ህዝብ ከመገንባት አንጻር ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

መድረኩ የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩም በአንድ ክልል ውጤታማ የሆነ ህግን ወደ ሌላ ክልል በመውሰድ ለመተግበር እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡    

በተጨማሪ እርስ በእርስ ልምድ ለመለዋወጥም መድረኩ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ገለጻ፤ በአዋጁ የተደነገጉት ስድስቱ የመንግስታት ግንኙነት መድረኮችን በሚፈለገው አግባብ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምድ ይዳብራል፡፡

የሚታዩ የጽንፈኝነት አዝማሚያዎችን በዘላቂነት ለመፍታትና በቀላሉ የሚፈቱ ችግሮች የህይወትና የንብረት መስዋዕትነት ሳያስከፍሉ ለመከላከል መድረኮቹ አስፈላጊ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የአገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚ አካላት ግንኙነትን አስመልክቶ ፅሑፍ ያቀረቡት አቶ ሙስጠፋ ናስር በበኩላቸው በግንኙነት መድረኩ በዋናነት የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች አባል የሚሆኑበትና እንደ አስፈላጊነቱም ሌሎች የህግ አካላት እንደሚካተቱም አብራርተዋል፡፡

በሚኖራቸው ግንኙነትም በዳኝነት ነጻነት እንዲሁም የፍትህ እና የዳኝነት ስርዓቱን ለማዘመን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት መግባባት ላይ የሚደርሱበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡      

በመድረኩ የተሳተፉት የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች በሰጡት ሃሳብም የተለያዩ ቴክኒክ ድጋፎችን ለመለዋወጥና ልምዶችን ለመጋራት የግንኙነት መድረኩ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡

አገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች የግንኙነት በሁሉም ክልሎች ፍትህን በእኩልነት ለማስፈን እንደሚያግዝም ነው የገለጹት፡፡