በኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ያሉ የውጭ ጫናዎችን ለመቀነስ በተሻለ የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶች ሊጠናከሩ ይገባል

108

ግንቦት 9/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ያሉ የውጭ ጫናዎችን ለመቀነስ በተሻለ የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2014 በጀት አመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ባለፉት 9 ወራት በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብትና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አብራርተዋል።

በፖለቲካ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉአላዊነት፣ በጋራ ጥቅምና እኩልነት ላይ የተመሰረት የውጭ ግንኙነት ላይ መሰረት በማድረግ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ አንዳንድ የምዕራብ አገራት ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ አለም አቀፍ ድርጅቶችና አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን በመንግስት ላይ ያልተገባ ጫና ለማሳደር ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን ጫና ለመቀነስና የዲፕሎማሲ ግንኙነቱ እንዲሻሻል ለማድረግ በስትራቴጂ ታግዞ ባከናወናቸው ተግባራት አወንታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በብዙ ወገን፣ በሁለትዮሽና በሌሎች የፖለቲካ ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ስራዎችንም አቶ ደመቀ በዝርዝር አስረድተዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም ሚኒስቴሩ የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን ተቋማዊና መዋቅራዊ ለውጥ አበረታች መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር በአሜሪካ  መንግስት የተረቀቁ ህጎችን በተመለከተ እና ለትግራይ ክልል አየተደረገ ያለውን ሰበአዊ ተደራሽነት በሚመለከት የምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ህጎች እንዳይጸድቁ ለማድረግ ዝርዝር የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ደመቀ አስረድተዋል።

ለትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ የጸጥታ ስጋት ሆኖ የቀጠለው አሸባሪው ህወሃት መሆኑንም ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል ግን ለሰብአዊነትና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለውጡን ተከትሎ ያደረገው መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጥ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ያሉ የውጭ ጫናዎችን ለመቀነስ በተሻለ የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዜጋ ተኮርና ዲፕሎማሲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው በመመለስ ያደረገውን ጥረት በማድነቅ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከምክር ቤቱ የተሰጡ አስተያየቶችን በግብአትነት በመውሰድ ሚኒስቴሩ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም