በአገር አቀፍ ደረጃ ለአንድ ወር የሚቆይ የመንገድ ደህንነት ቁጥጥር ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

123

ግንቦት 9/2014/ኢዜአ/ በአገር አቀፍ ደረጃ ለአንድ ወር የሚቆይ የመንገድ ደህንነት ቁጥጥር ንቅናቄ እንደሚካሄድ የመንገድ ደህንነት እና የመድህን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።

ንቅናቄው ከነገ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበር ሲሆን ፤ በዚሀም በአገር አቀፍ ደረጃ አደጋ በብዛት በሚከሰትባቸው 150 አካባቢዎች ላይ ልዩ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ንቅናቄው በዋናነት በትራፊክ አደጋ የሚከሰትን ሞት፣ የአካል መጉደልና ንብረት ውድመት መቀነስ ነው፡፡

የመንገድ ደህንነት እና የመድህን  ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ  ንቅናቄው ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

በዚህም በተለይ በመጪው ክረምት ወቅት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአሽከርካሪዎች የስነ-ምግብር ጉድለትና ቸልተኝነት እንዲሁም የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ችግሮች ለትራፊክ አደጋ መከሰት ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም በበጀት ዓመቱ  በተደጋጋሚ የህግ ጥሰት በፈጸሙ 1 ሺህ 886 አሽከርካሪዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

ይህን የህግ የማስከበር ተግባር በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ተሽከርካሪ ደህንነት ማስጠበቅ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፌዴራል ፖሊስ ትራፊክ የመንገድ ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደነቀ ክፍሌ በበኩላቸው የመንገድ ደህንነት ቁጥጥር ስራዎች ስኬታማ መሆን የሚችሉት ከጸጥታ አካላት በተጨማሪ ኀብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የመንገድ ድህንነትን ከማስጠበቅ ባሻገር ጥፋተኞች ለህግ እንዲቀርቡ በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

እየተከናወኑ ባሉ የመንገድ ደህንነት ስራዎች አማካኝነት ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለአብነትም በ2010 ዓ.ም በ10 ሺህ ተሽከርካሪዎች በአማካኝ ይመዘገብ የነበረውን የ55 ሰዎች ሞት በ2013 ዓ.ም ወደ 32 ነጥብ 6 ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም ይህን አሃዝ ወደ 30 ለማውረድ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡