በወረኢሉ ወረዳ ከ500 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የግብርና ምርምር ማዕከል ሊገነባ ነው

201

ደሴ፣ ግንቦት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ ከ500 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የግብርና ምርምር ማዕከል ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ችሎት ይርጋ እንደገለፁት፤ የማዕከሉን ግንባታ በ5 ዓመት ለማጠናቅቅ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል።

ጎን ለጎን የአስተዳደርና የላብራቶሪ ህንጻዎች ግንባታ ይከናወናል በማለት ገልፀው፤ ማዕከሉ የእንሰሳት፣ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ከግብርናው ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ጉዳዮች ሁሉ ለመመራመርና ምርታማነትን ለማሳደግ ታልሞ የሚገነባ መሆኑን አመልክተዋል።

መሰረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው የምርምር ማእከላትን በማጠናከር ከድህነትና ከጠባቂነት ለመላቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ግብርናውን ማዘመን፣ በጥናትና ምርምር አጠናክሮ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።የማዕከሉ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ በጥራት ተጠናቆ ስራ እንዲጀምር ሚኒስቴሩ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ግብርናውን በጥናትና ምርምር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ምርምር ማዕከሉ ተጠናቆ ስራ እንዲጀመር ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበው፤ አርሶ አደሩ አጋጣሚውን እንዲጠቀምም አስገንዝበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው ማዕከሉ በጥራት እንዲገነባ አስተዳደሩ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የምርምር ማዕከል እንዲገነባለት ሲጠይቅ መቆየቱን አስታውሰው፤ የለውጡ አመራር ለጥያቄ መልስ መስጠቱን ገልጸዋል።

ለምርምሩ 100 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ጠቁመው ዓላማው እንዲሳካ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም